ቅዱስ ያሬድ ማነው? ከዳንኤል ክብረት
የቅዳስ ያሬድ አባቱ አብድዩ /ይስሐቅ/ እናቱ ክርስቲና /ታውክልያ/ ይባላሉ /በሌላም በኩል አባቱ እንበረም እናቱ ትውልያ ይባላሉ የሚል ታሪክም አለ፡፡/ የትውልድ ሥፍራው አከሱም ነው፡፡ የተወለደው በ505 ዓ.ም/ ሚያዝያ 5 ቀን የሚል አለ/ ሲሆን በተወለደ በ7 ዓመቱ ወላጅ አባቱ ስለሞተ እናቱ የአክሱም ጽዮን መምህር ለነበረው ለአጎቱ ለጌዴዎን እያስተማረ እንዲያሳድገው ሰጠችው፡፡ ከአባ ጌዴዎንም ዘንድ እየተማረ ለ25 ዓመት ተቀመጠ፡፡ ሆኖም ቃለ እግዚአብሔር የመቀበል ችሎታው ደካማ ስለሆነ በጣም ያዝን ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ከትምህርት ድክመቱ የተነሣ አጎቱ በጨንገር ቢገርፈው በዚህ ተበሳጭቶ ትምህርቱን ትቶ ሄደ፡፡ በመንገድም ሲጓዝ ውሎ በቀትር ደክሞት ከዛፍ ሥር ዐረፈ፡፡ በዚያ ጊዜ አንድ ትል ከዛፉ ላይ ያለውን ፍሬ ለመብላት ስድስት ጊዜ በመውደቅና በመነሣት ዛፉ ላይ ለመውጣት ሞክሮ በሰባተኛው ሰተት ብሎ ወጥቶ ሲበላ ተመለከተ፡፡ እርሱም በፈጸመው የብስጭት ተግባር በመጸጸት ተመልሶና አጎቱን ይቅርታ ጠይቆ ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ አጎቱም ተደስቶ ዓይነ ልቡናውን ያበራለት ዘንድ እያለቀሰ ፈጣሪውን ለመነለት፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ለቅዱስ ያሬድ ዕውቀትን ገልጾለት መጻሕፍተ ብሉያትንና ሐዲሳትን ዐወቀ፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይህን በተመለከተ ሰላም ለያሬድ ስብሐተ መላእክት ለሕዋጼ እንተ አዕረገ በልቡ ኅሊና መንፈስ ረዋጼ ለትምህርተ መጽሐፍ ገብአ እምኀበ ኮነ ነፋጼ በብዙኀ ፃማ ዘአልቦ ሐጻጼ መልዕልተ ዕፅ /ኮሞ/ ነጸሮ እንዘ የዐርግ ዕጼ የሚል ዐርኬ ደርሰውለታል፡፡ ይህን አርኬ የድጓ መምህራን ጠዋት ጉባኤ ሲዘረጉ ተማሪዎቻቸውን ያስደርሷቸዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ወደ መምህሩ ተመልሶ ትምህርቱን ቀጠለና ቅዱሳት መጻሕፍትን በሚገባ አጠና፡፡ ሢመተ ዲቁና...