«በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፤ ወደ እኔም እንዳመጣችሁ አይታችኋል!»


ንስር ንጉሠ አዕዋፍ ነው፤ በመብረርም ፈጣንና ጠንካራ የሆነ ነው፡፡ ረዥም ዘመን የሚኖር፣ ከሩቅ አጥርቶ የሚያይ፣ እስከ ተራሮች ከፍታና ከደመናት በላይ ለመብረር የሚያስችሉ ኃያላን አክናፍ ያሉት ነው፡፡ እንዲሁም ንስር ለጫጩቶቹ ርኅሩኅ ነው፡፡ በጥበብ ይንከባከባቸዋል ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙም ያለማምዳቸዋል፡፡

ከእነዚህ ተነጻጻሪ ባሕርያት የተነሣ እግዚአብሔር በትሕትና ራሱን ከንስር ጋር አመሳስሏል፡፡ እግዚአብሔር ዘላለማዊ፣ ሁሉን ቻይ፣ ሁሉን ተመልካች (ሁሉን የሚያይና የሚያውቅ የጥበብ ምንጭ)፣ ምሕረትን የተሞላ፣ ለሕዝቡ የሚራራና ወደ ድኅነት የሚመራቸው ነው፡፡

ጌታ እግዚአብሔር ሕዝቡን መርቶ ከግብፅ ባወጣቸውና ከፈርኦን ሠራዊት ጠብቆ በተአምር ቀይ ባሕርን ባሻገራቸው ጊዜ እንዲህ ብሏቸው ነበር፡- ‹‹በግብፃውያን ያደረግሁትን በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል›› (ዘጸ. 19፥4)፡፡

በንስር ሕይወት ውስጥ ካሉት ምሥጢራት አንዱ ሁልጊዜ ጎጆውን በከፍታ ላይ መሥራቱና በአለታማ ቋጥኞችና ምሽጎች ውስጥ መኖሩ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለኢዮብ ጥበቡንና ኃይሉን ሲያሳየው ያለውን ልብ በሉ፤ ‹‹በአፍህ ትእዛዝ ንስር ከፍ ከፍ ይላልን? ቤቱንስ በአርያም ላይ ያደርጋልን? በገደል ላይ ይኖራል፤ በገደሉ ገመገምና በጥጉ ያድራል፡፡ በዚያም ሆኖ የሚነጥቀውን ይጎበኛል፤ ዓይኑም በሩቅ ትመለከታለች፡፡›› (ኢዮ.39፥27)

ንስር ስለምን ከፍ ብሎ ጎጆውን በተራሮች ጫፍ ላይ ይሠራል?

እንደ አዳኞችና አራዊት ያሉ ጠላቶቹ ሊደርሱበት ከማይችሉበት ስፍራ ለመገኘት ብሎ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ወደ ጎጆው ደርሶ ጫጩቶቹን ሊበላበት የሚችል ሌላ ጠላት አለ፡፡ ይህም ጠላት እስከዚያ ከፍታ ድረስ እስኪደርስ በልቡ ሊሳብ የሚችለው ዕባብ ነው፡፡

ታዲያ ይህንን ውስብስብ ችግር ንስር እንዴት ይፈታዋል?

ዕባቡ ዘልቆ እንዳይገባ ጎጆውን በመጠን ብዙ በሆኑ እሾኆች ከውጪ በኩል ያጥረዋል፡፡ የጎጆው ውስጠኛ ክፍል ደግሞ በላባዎች የተደራጀ ሞቃታማና ምቹ ነው፡፡ ውጪው ግን በእሾኽ የታጠረ ነው፡፡ ታላቁ ንስር ለጫጩቶቹ ጥሩ እንክብካቤ ያደርጋል፡፡ የሚበሉትን ያቀርብላቸዋል፤ በክንፎቹ እያንዣበበ ይጋርዳቸዋል፤ በአፉ (በመንቆሩ) ይመግባቸዋል፡፡ ትንንሾቹ አንስርት (ንስሮች) እንዳሻቸው እንዲኖሩ የተተዉ ቢሆኑ ኖሮ ለዘላለም ከጎጆአቸው ባልወጡ ነበር፡፡

ስለዚህ ጊዜው ደርሶ ጫጩቶቹ ሲያድጉ ታላቁ ንስር የመብረር ችሎታቸውን ይፈትናል፤ ጎጆውንም መትቶ ያነቃንቀዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ መገፋቱ ጠንከር ሲል ጎጆው ከተራራው ጫፍ ወደ ዝቅተኛው ጫፍ ሊወድቅ ይችላል፡፡

ጎጆው በተነዋወጸ ጊዜ ከውጪ ያሉት እሾኾች ወደ ውስጥ ይገባሉ፤ በጫጩቶቹም ላይ መወጋትንና ሕመምን ያስከትላሉ፡፡ ክንፎቻቸውን ያንቀሳቅሳሉ ለመብረርም ይሞክራሉ፡፡ ከተሳካላቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ለመብረርና ንጹሑን የሰማይ አየር እየተነፈሱ ለመደሰት ይችላሉ፤ ዳግመኛም ወደ ጎጆአቸው በፍጹም አይመለሱም፡፡ በዚህም ተልእኮውን በሚገባ ያለችግር በማከናወኑ ታላቁ ንስር ደስታ ይሰማዋል፡፡

የጫጩቶቹ የክንፋቸው ላባ በበቂ ሁኔታ ካላደገና መብረር ሳይቻላቸው ከወደቁ ታላቁ ንስር ፈጥኖ ክንፎቹን ዘርግቶ ይይዛቸዋል፤ በክንፎቹም ይሸከማቸዋል፡፡ ለተጨማሪ ቆይታም ወደ ጎጆአቸው ይመልሳቸዋል፡፡ ይህንን ዑደት መብረር እስከሚችሉ ድረስ ይደጋግመዋል፡፡ አይደንቅም ትላላችሁ?

‹‹ንስር ጫጩቶቹን እንደሚያወጣ በእነርሱም ላይ እንደሚሰፍፍ ክንፎቹን ዘርግቶ ወሰዳቸው፤ በክንፎቹ አዘላቸው፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ብቻውን መራው›› ዘዳ.33፥10

ከላይ እንደተገለጠው እግዚአብሔር ራሱን ከንስር ጋር አመሳስሏል፡፡ እኛም ከድንቅ ፍጥረቱ ከንስር ሕይወት አንዳንድ ቁም ነገሮችን እንቀስማለን፡፡

ምእመናን የንስር ጫጩቶችን ይመስላሉ!

የንስር ጫጩቶች ደካሞችና በራሳቸው ለመቆምና በራሳቸው ለመኖር የማይችሉ ናቸው፡፡ የሰው ልጅም ሲወለድ በራሱ መብላት መጠጣት፣ መሄድ፣ መናገር፣ ማሰብ፣ ፍላጎቶቹን መፈጸም የማይችል ሆኖ ነው የሚወለደው፡፡ በተመሳሳይ በመንፈሳዊ ሕይወቱም ጠላቶቹን፣ ኃጢአትን፣ ሰይጣንን፣ የሥጋ ምኞትንና የዚህችን ዓለም መስህብነት ለመቃወም ደካማ ነው፡፡

ነቢዩ ንጉሥ ዳዊት ይህንን እውነታ ከአስከፊው ውድቀቱ በኋላ በስድስተኛው መዝሙሩ ሲገልጥ ‹‹አቤቱ በቊጣህ አትቅሠፈኝ በመዓትህም አትገሥጸኝ፡፡ ድዉይ ነኝና አቤቱ ማረኝ›› ብሏል፡፡ (መዝ.6፥1-2) የእግዚአብሔር ንቁ ዓይኖች፣ ኃያላን ክንዶቹና ሁልጊዜ በላያችን የሚጋርዱን ክንፎቹ ያስፈልጉናል፡፡ ይህንን ደካማነታችንንና ኃጢአተኛነታችንን እስካላመንን ድረስ ግን የእግዚአብሔር ኃይል ወደ እኛ ፈጽሞ አትመጣም፡፡

በሌላ ያማሩ ቃላት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በሰማያት ላይ ለረድኤትህ በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም፡፡ መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው ፤ የዘላለም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፡፡››
(ዘዳ.33፥26)
የንስር ጫጩቶች እንደ እኛ አላዋቂዎች ናቸው፡፡ እኛ ከትምህርታችንና ከዲግሪዎቻችን ያገኘነው ምንም ይሁን ምን አላዋቂነታችንንና የእግዚአብሔር መሪነት እንደሚያስፈልገን ማመን ይገባናል፡፡ በመንፈሳዊው ዕይታ የሰው ልጅ አላዋቂ ነው፡፡ ወደፊት ስለሚመጣው ነገር፣ ከሞት በኋላም ስላለው ነገር፣ ሌላው ቀርቶ ስለ ራሱና በፍጥረታት ውስጥ ስላሉ በሚልዮኖች ስለሚቆጠሩ ነገሮች እንኳን አያውቅም፡፡ ማየት የማይችል ከመሆኑም የተነሣ የቃለ እግዚአብሔርና የመንፈስ ቅዱስ ብርሃንነት እንዲሁም ምክረ ካህን ያስፈልገዋል፡፡

እግዚአብሔር እኛን የሚንከባከብበት መንገድ ከንስር ጋር ይመሳሰላል!

ንስር ከፍ ከፍ እንደሚልና ጎጆውን በከፍታ ላይ እንደሚሠራ እግዚአብሔርም ልጆቹ ከሌላው ሰው በተለየ መዓርግ እንድንኖር ይፈልጋል፡፡ በቅድስና ሕይወት እንድንኖርና ከእርሱ ጋር ለዘላለም በመንግሥቱ ለመኖር ራሳችንን እንድናዘጋጅ ይፈልጋል፡፡ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ በጥምቀት ከተወለድን ጀምሮ የመንግሥተ ሰማያት ዜጎች ሆነናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 3፥20፡ ‹‹እኛ ሀገራችን በሰማይ ነውና›› ብሏል፡፡ ከሰማያዊው አምላክ ተወልደናል፤ ምግባችን ቃለ እግዚአብሔርም፣ ሥጋ ወደሙም፣ ጸሎትና አንድነታችንም ሁሉም ከላይ ነው፡፡ ‹‹በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፤ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ›› (ያዕ.1፥18)፡፡

ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም፡፡ ሞታችኋልና ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና ሕይወታችሁ የሆነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ በዚያን ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችሁ›› (ቈላ. 3፥1-4)፡፡

እግዚአብሔር ጎጆአችንን በእሾኾች ያጥረዋል!

በእርግጥ እግዚአብሔር ጥቂት እሾኾች እንዲያቆስሉን ያደርጋል፤ ይህም ፍቅሩንና ለእኛ ማሰቡን የሚያስረዳ ነው፡፡ በእሾኽ እንድንወጋ የሚፈቅደው በቁስላችን፣ በስቃያችንና በሕመማችን ስለሚደሰት አይደለም፤ በዚህ ስቃይ እንድናድግና እንድንጎለምስ ሊያስተምረንና ሊያለማምደን ነው እንጂ፡፡ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ስቃይና መከራ አልቀረለትም፤ እንዲያው በተገላቢጦሹ እስከ መጨረሻው መራራ ጽዋን ጠጣ፡፡ እንዲህ ተብሎ ስለ እርሱ እንደተጻፈ፡- ‹‹ምንም ልጅ ቢሆን ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ (ዕብ. 5፥8)››

ሌሎችን የመፈወስ ጸጋ የተሰጠው ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ ‹‹በሥጋው ላይ ስለነበረበት እሾኽ›› አቤቱታ አሰምቶ ነበር፡፡ እንዲህ ማለቱን ልብ በሉ፡ ‹‹ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መውጊያ ተሰጠኝ ይኸውም እንዳልታበይ ነው፡፡ ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ፡፡ እርሱም ፡- ጸጋዬ ይበቃሃል ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ፡፡ እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ፡፡ ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና›› (2ቆሮ. 12፥7-10)፡፡

‹‹ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው፡፡ ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና (ሮሜ. 8፥20-22)››

ስለዚህ እግዚአብሔር በእነዚህ እሾኾች እኛን በማሰቃየት ደስታን የሚያገኝ ሆኖ አይደለም፤ ይህ ለድኅነታችን አስፈላጊና ወሳኝ የሆነ ልንሸከመው የሚገባን መስቀል ስለሆነ ነው፡፡ ንስር ልጆቹን ከዕባብ ለመጠበቅ ጎጆውን በእሾኽ እንደሚያጥር እግዚአብሔርም ከቀደመው ዕባብ ከዲያብሎስ እጅ ይጠብቀን ዘንድ በሕይወታችን ውስጥ ጥቂት እሾኾች እንዲኖሩ ይፈቅዳል፡፡ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ‹‹ለምን?›› ብለን እንጠይቀዋለን፡፡ እርሱም እንዲህ ሲል ይመልሳል፡- ‹‹እኔ የማደርገውን እናንተ አሁን አታውቁም በኋላ ግን ታስተውሉታላችሁ›› (ዮሐ.13፥7፣ መዝ. 72፣ ዕብ.12)፡፡

ንስር ጎጆውን እንደሚያናውጽ እግዚአብሔርም እንዲሁ ያደርጋል!

እሾኾች ጫጩቶቹን ለመብረር እንዲገፋፉ ለማድረግ ሲል ንስር ጎጆውን ያነዋውጻል፡፡ ይህ ዓይነተኛ ፈተናና ትምህርት ነው፡፡ በእኛም እንዲሁ ነው፤ እግዚአብሔር ጎጆአችንን በኃይል ያነዋውጸዋል፤ ይሁናና በፍጹም አያፈርሰውም፡፡

ይህ ንውጽውጽታ ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሣ ሊያስደነግጥ ይችላል፤ ይሁንና አትጨነቁ ዓላማውንም አትዘንጉ፡፡ እንድትበርሩ ሊያስገድዳችሁ ነው፤ አዎን በሰማያዊው ህዋ ደስ እንድትሰኙ ሊያደርግ ነው፡፡ በዘመናችን የሚከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥና ዓውሎ ነፋስም የብዙዎችን ጎጆ የሚያናውጽና ሰዎችን ለንስሓ ለማዘጋጀት የሚደረግ የማንቂያ ጥሪ አንዳች ማሳያ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በመንግሥቱ ለዘላለም የምንኖርበትን ዘላለማዊ ጎጆ አዘጋጅቶልናል፡፡ ስለዚህም ሰነፎችና ከዚህች ዓለም ጋር የተሳሰርን እንድንሆን አይፈልግም፡፡ ይህን ታላቅ ተስፋ በልባችሁ አኑሩ፤ ምድራዊ ስቃይን ሁሉ ትዘነጋላችሁ፡፡ ‹‹የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ›› በእናንተ ዘንድ እንዳለም አስታውሱ (ቈላ. 1፥27.)፡፡ ከዚህ ተግባር ጠቀሜታዎች አንዱ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔርን በመተማመን መጠባበቅንና ኃይልን ማደስን እንደ ንስር በክንፍ መውጣትን›› የምንማር መሆናችን ነው (ኢሳ. 40፥31)፡፡ እርሱ ‹‹መንግሥትህ ትምጣ›› ብለን እንድንጸልይ አስተምሮናል፡፡ እናም አንድ ቀን ወደ ሰማይ እንነጠቃለን፤ ወደ ምድራዊው ጎጆአችንም በፍጹም አንመለስም፡፡

ክንፎቹን ዘርግቶ ይሸከማቸዋል!

መዝሙር 90 ይህንን እውነታ በሰፊው ያስረዳል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ፈጣን እርዳታ፣ ስለ መግቦቱ፣ ጥበቃውና አድኅኖቱ ይናገራል፡፡

‹‹በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል፡፡ … እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና፡፡ በላባዎቹም ይጋርድሃል፤ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፤ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል›› /መዝ. 90፥1-5/፡፡

ቀሲስ አውግስጢኖስ ሀና /ግብፃዊ/
ትርጉም ፡ ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ST. JHON / Monthly Magazine of Coptic Orthodox Church.
Vol. 17 no. 190 November 2005




ጌታችን በምሳሌ
በኅሩይ ስሜ

በወንጌል ትርጓሜ ትምህርት ሶምሶን የጌታችን ምሳሌ እንደሆነ ተጽፎአል፡፡ /ማቴ.2÷23/፡፡ ይህንንም ምሳሌነቱን ሲያስረዳ «ሶምሶን በተናቀች የአህያ መንጋጋ ጠላቶቹን እንደ አጠፋ ጌታም አይሁድ፣ መናፍቃንና አጋንንት በናቁት ሞቱ ሞትን አጥፍቷል፡፡ ሶምሶን በሕይወተ ሥጋ ሳለ ካጠፋቸው አሕዛብ በሞቱ ያጠፋቸው እንዲበዙ፤ ጌታም በሕይወተ ሥጋ ሳለ ካጠፋቸው አጋንንት በሞቱ ያጠፋቸው ይበዛሉ» በማለት ያመጣዋል፡፡ ስለሆነም የሶምሶን ታሪክ በብሉይ ዘመን የተፈጸመ ቢሆንም ሊመጣ ያለውን የጌታን ሥራ ያሳይ የነበረ ሥውር ሐዲስ መሆኑን አንድምታው ይመሰክራል፡፡ በዚህም አባቶች አንዱን አንቀጽ ብቻ ነጥለው የተነተኑት የሶምሶን ታሪክ ብዙ ምስጢርና ትርጓሜ እንዳለው ለማየት ችለናል፡፡ የሶምሶን ሙሉ ታሪኩም ለጌታችን ምሳሌ የሚሆን ነገር እንዳለበት ያስረዳናል፡፡ ይህንንም ዝርዝር ታሪኩን በማጥናት መረዳት ይቻላል፡፡

ገና ጥንት ሶምሶን ከመወለዱ በፊት በመጽሐፈ መሳፍንት በምዕራፍ 13÷1 ላይ እንደተጻፈው የእስራኤል ሕዝብ በሠሩት ኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልተው ስለነበር በጠላቶቻቸው በፍልስጤማውያን ይገዙ ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከመወለዱ በፊት የሰው ልጆች ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልተው ይኖሩ ነበር፡፡ ኃጢአትም በምድር ላይ ከመንሰራፋትዋ የተነሣ አጋንንት ሰዎችን ሠልጥነውባቸው በሲኦልና በመቃብር ይገዙዋቸው ነበር፡፡ ይህም የሶምሶን መወለድ ሕዝበ እስራኤል ለፍልስጥኤማውያን ባርያ ከመሆን የሚድኑበት የእግዚአብሔር መንገድ ነበር፡፡ ይልቁንም ደግሞ የሰው ነፍስ ለዲያብ ሎስ ባርያ ከሆነችበት ለሚያድናት ለመድኃኒታችን ምሳሌ ነበር፡፡

በዚያን ዘመን እግዚአብሔር ለሕዝቡ ነጻነትን ሊሰጥ በወደደ ጊዜ መልአኩን ከነገደ ዳን የነበረ ማኑሄ ወደሚባል ካህን ሚስት ሰደደ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ለሚስትየው ተገልጦ «አንቺ መካን ነሽ፤ ልጅም አልወለድሽም፤ ነገር ግን ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፡፡ አሁንም ተጠንቀቂ የወይን ጠጅን የሚያሰክርም ነገር አትጠጪ፡፡ ርኩስም ነገር አትብዪ . . . ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት» አላት፡፡ ሶምሶን በመልአኩ ለጊዜው ናዝራዊ ቢባልም ፍጻሜው ግን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለአምላካችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ማቴ. 2÷23 አንድምታ፡፡

የማኑሄ ሚስትም መልአኩ የነገራትን ነገር መጥታ ለባለቤትዋ ነገረችው፡፡ በድጋሚም ማኑሄ በቅርብ ባለበት መልአኩ ተገልጾ እንደገና አስቀድሞ የተናገረውን ደገመላቸው፡፡ ብዙም ሳይቆይ መካኒቱ የማኑሄ ሚስት ጸነሰች፡፡ በመልአኩ ብስራትም ሶምሶን ተወልዶአል፡፡ በኋለኛው ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን መጥቶ፤ «ማርያም ሆይ፤ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋን አግኝተሻልና አትፍሪ እነሆም፤ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ» ብሎ ካበሰራት በኋላ አምላካችን ተወልዷል /ሉቃ. 1÷30-32/፡፡ በመሆኑም አስቀድሞ በመልአኩ ብስራት የተወለደው ሶምሶን በኋለኛ ጊዜ በቅዱስ ገብርኤል መልአክ ብስራት ለሚወለደው ለጌታችን ምሳሌ ነው፡፡

ሶምሶን በሕገ እግዚአብሔር ማለትም በናዝራውያን ሕግ /ዘኊል 6÷1-4/ በተሠራው ሕግ መሠረት ወይን ጠጅ ሳይጠጣ ጠጉሩን ሳይላጭ ያድግ እንደነበር ሁሉ አምላካችንም ሥጋ ጠባይዐዊን በተዋሕዶ ቢነሳም ለባሕርዩ ኃጢአት አይስማማውምና ጽድቅን ብቻ አድርጓል፡፡ ነገር ግን ፍጹም በተዋሕዶ መክበሩን ሲያጠይቅ የኦስሪቱን ሕግ እየፈጸመ ለእስራኤል እስኪገለጥ ድረስ በጥበብና በቁመት በሞገስም እያደገ መጥቷል /ሉቃ. 2÷52/፡፡

ሶምሶንም ባደገ ጊዜ ከደጋው የእስራኤል አገር /ከፍተኛ ቦታ/ ወደ ቆላ /ዝቅተኛ ቦታ/ ወደ ሆነው ወደ ተምና ሔደ፡፡ በዚያም የአንበሳ ደቦል እያገሣ መጣበት፡፡ ሶምሶንም የእግዚአብሔር መንፈስ ኃይል ሆኖት ጠቦትን እንደሚገነጣጥል መሣሪያ ሳይኖረው በእጁ ብቻ ገደለው /መ.መሳ. 14÷4-9/፡፡ ከተምናም ሀገር ወደ ቤቱ ሲመለስ ወደ ገደለው የአንበሳ ሬሳ ሄደ፤ ተመለከተም፡፡ በውስጡም ንብ ሰፍሮ ማር ሠርቶ ነበር፡፡ ስለዚህም ያገኘውን ማር ወስዶ እየበላ በመንገዱ ሄደ፡፡ ለእናትና አባቱም አምጥቶ ሰጣቸው፡፡ ወልደ እግዚአብሔር ክርስቶስም ከሰማየ ሰማያት ከፍ ካለው የክብር ዙፋኑ ወደ ምድር በወረደ ጊዜ ዲያብሎስ በአይሁድ ላይ አድሮ እያገሳ /ስቀለው . . . ስቀለው እያስባለ/ መጣ /ሉቃ. 4÷13/፡፡ ዲያብሎስም የሚያገሣ አንበሳ ተብሎ የተገለጸውን ግብሩን ፈጸመ /2ጴጥ.5÷9/፡፡ አምላካችን ግን አንዳች የመለኮቱን ኃይል ሳይገልጥ ተገርፎና ተቸንክሮ በመስቀል ላይ ውሎ ዲያብሎስን ያዘው፡፡ በነፋስ አውታርም ወጠረው፤ በእሳት ዛንጅር አሰረው፡፡ በብርሃነ መስቀሉም ራስ ራሱን ቀጥቅጦ በተናቀው ሞቱ ድል አደረገ፡፡ ከሲኦል ውስጥም አምላክ እንደማር የሚጣፍጠውንና በመስቀል ላይ «ተጠማሁ» ብሎ የመሰከረለትን የሰው ነፍስ አወጣ፡፡ የሰውን ልጅ ነፍስ ማርኮ አወጣ፡፡ ስለዚህ ሶምሶን ለጌታችን በረቀቀ ምስጢር ምሳሌ ነው፡፡

ከዚያም ሶምሶን ወደ ሰርግ ቤት መጣ፡፡ ሠላሳ ሚዜዎችም ተሰጡት፡፡ በዚያም ደስታ ተድላ አደረገ፡፡ ጌታችንም ሠላሳ ዓመት በሞላው ጊዜ ለሰርግ እንደሚወጣ ሙሽራ ወንጌልን መስበክ ጀመረ /ዮሐ. 3÷29/፡፡ የመጀመሪያውንም ተአምር በቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት ውስጥ አደረገ፡፡ /ዮሐ. 2÷11/፡፡ ለሰው ልጆችም ድኅነትን፣ ፈውስን ሰጠ በዚህም ለሰው ሁሉ ተድላ ደስታን አደረገ፡፡ ስለዚህም ሠላሳ ሚዜዎቹ የጌታችን እድሜ ምሳሌዎች ተድላ ደስታ ማድረጋቸውም የወንጌል ስብከት ምሳሌና የጌታችን መገለጥ አብነት በመሆኑ ለጌታችን ምሳሌዎች ናቸው፡፡

የሰርጉም ቀናት ከማለቁ በፊት ሶምሶን ለፍልስጤማውያኑ ሚዜዎች እንቆቅልሽ ተናገራቸው፡፡ እንቆቅልሹም በአንበሳው ላይ ስለ አደረገው ነበር፡፡ ሚዜዎቹም ወደ ሚስቱ ሔደው «ያለንን ልታስወስጅብን አንቺና ባልሽ ወደ ሰርጋችሁ ጠርታችሁናልና የእንቆቅልሹን መልስ ንገሪን» አሉዋት፡፡ እንቆቅልሹንም ካልፈቱ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስ ለሶምሶን ሊሰጡ ተዋውለው ነበር፡፡ ጌታችንም በምሴተ ሐሙስ ክቡር ሥጋውን ቅዱስ ደሙን ለሐዋርያት በሰጠ ጊዜ ሰይጣንና አይሁድ ወደ ይሁዳ ቀርበው ጌታህ የያዝነውን ሥልጣን ሊያስለቅቀን ይፈልጋልን) አሉ፡፡ አንድም ዲያብሎስ የያዝኩትን የሰውን ነፍስ ሊያስለቅቀኝ ይፈልጋልን) አለ፡፡ አንድም አይሁድ /ፈሪሳውያን ሰዱቃውያን/ ያየዝነውን ሥልጣን ሊያስለቅቀን ይፈልጋልን አሉት /ማቴ.21÷23፣ ዮሐ. 11÷48፣ ዮሐ.14÷16፣ ዮሐ. 12÷19/፡፡

ይሁዳንም አውቀን ጌታህን እንድንይዘው ምልክትን ስጠን አሉት፡፡ እርሱም «ሒጄ የምስመው ክርስቶስ ነው» አላቸው /ማቴ. 26÷48-49/፡፡ ጌታችንም ከወንጌላዊው ዮሐንስ ጋር ይመሳሰል ነበርና ሁለቱን ለይቶ የሚያሳያቸውን፤ እንቆቅልሽ የሆነባቸውንም ይህንን ነገር የሚገልጽላቸው ሰው ይፈልጉ ነበር፡፡ ይሁዳም ይህንን ለማድረግ የተስማማው በሠላሳ ብር ነበር፡፡ በመሆኑም የሶምሶን ሚስት የይሁዳ ምሳሌ፣ ሠላሳው በፍታ ቀሚስ ይሁዳ ሊሸጠው ለተሰማማበት ለሠላሳው ብር ምሳሌ፤ ፍልስጥኤማውያኑ /የአይሁድ፣ የዲያብሎስ/፤ ሶምሶን የጌታችን ምሳሌዎች ናቸው፡፡

በሰባተኛውም ቀን ሚስቱ ምስጢሩን አውጥታ ለፍልስጥኤማውያን ሚዜዎቹ ሰጠች፡፡ እነርሱም «ከአንበሳ የሚበረታ ከማር የጣፈጠስ ምንድን ነው?» ብለው እንቆቅልሹን ፈቱበት፡፡ ሶምሶንም ተቆጣ ወደ አስቀሎንም ወረዶ ሠላሳ ሰዎችን ገድሎ በፍታውን ሰጣቸው፡፡ ወደ ሀገሩም ሄዶ ተቀ መጠ፡፡ በስንዴ መከር ጊዜ ወደ ሴቲቱ ዳግመኛ መጣ፡፡ አባትዋ ግን ለሚዜው አጋብቷት ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ ሶምሶን ሦስት መቶ ቀበሮዎች ሰብስቦ ችቦ በጭራቸው እያደረገ በእሳት ከለኮሰው በኋላ በደረሰው ስንዴ ላይ ለቀቀው፡፡ የሀገሩን መከር ሁሉ አቃጠለ፡፡ ከዚህ የተነሣ ፍልስጥኤማውያኑ ሴቲቱንና አባትዋን አቃጥለው ሶምሶንን ሊወጉ ወደ ይሁዳ ወጥተው ሰፈሩ /መ.መሳ. 15÷1-9/፡፡ የይሁዳ ሰዎች ወገኖቹም መጥተው «ፍልስጥኤማውያን ገዢዎቻችን ሳሉ ይህንን ለምን አደረግህ? አሁንም አስረን ለነርሱ አሳልፈን ልንሰጥህ ነው?» አሉት፡፡ እርሱም «እናንተ አትግደሉኝ እንጂ ለእነርሱ ስጡኝ» አላቸው፡፡ አስረውም ለፍልስጥኤማውያን ሰጡት፡፡

ጌታችንም በቃሉ ትምህርት እየሰበከ በእጁ ታምራት እያደረገ ብዙ አጋንንትን አጠፋ፤ ወንጌልን አስተማረ፡፡ በዚህም ጊዜ አይሁድ ቀርበው በገመድ አስረው ወሰዱት፡፡ ይገዙዋቸው ለነበሩት ለአሕዛብ ለሮማውያን አሳልፈው እንዲሰጡት ወሰኑ፡፡ ጲላጦስም «ወገኖችህ ለኔ አስረው አሳልፈው ሰጥተውሃል ምን አድርገሃል)» እያለ ከጠየቀው በኋላ እናንተው ግደሉት ሲል ለአይሁድ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ እነርሱም «ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንምና አንገድለውም» አሉ፡፡ /ዮሐ.18÷28-32/፡፡ በዚህም ሶምሶን ለጌታ ምሳሌ ነው፡፡

ሶምሶንንም አሳልፈው ለአሕዛብ ለፍልስጥኤማውያን በሰጡት ጊዜ በተናቀችው በአህያ መንጋጋ ሺሕውን ገድሎ ድል እንዳደረገ ሁሉ፤ ጌታችንም አሳልፈው ለአሕዛብ ለሮማውያን በሰጡት ጊዜ በተናቀችው በመስቀል ሞቱ ዲያብሎስን አጥፍቶታል፤ ሞትንም ድል አድርጓልና ሶምሶን ለጌታ ምሳሌ ነው፡፡ ሶምሶንም ከሌሒው ጽኑ ተጋድሎው በኋላ እስከሞት ድረስ እንደ ተጠማና እንደ ደከመ፤ የእግዚአብሔርንም ስም ጠርቶ ውኃ እንደፈለቀለት፤ ከሞትም ተርፎ በሕይወት እንደ ኖረ ሁሉ፤ ጌታችንም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሞ ከአጋንንት ጋር ተዋጋ፤ በአርባኛውም ቀን እጅግ ተራበ ተጠማም፡፡ የሥጋውን መጎዳትና መድከም የተመለከተው ዲያብሎስም ወደ እርሱ ቀርቦ «ይህንን ድንጋይ ዳቦ አድርገህ ብላ» ብሎ ቢፈትነውም «ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም» በማለት ድል አድርጎታል /ሉቃ. 4÷3-5/፡፡

በሶምሶን ላይ ያደረ ጸጋ እግዚአብሔር ስለነበር ፍልስጥኤማውያን በፍጹም ሊይዙት አልተቻላቸውም፡፡ በጋዛም በሌሒም ከሚሠራው የኃይል ሥራ የተነሣ በእጃቸው ሊገባ አልቻለም፡፡ ሊቋቋሙት እንደማይቻላቸው ባዩ ጊዜ አዘኑ፤ ተከዙ፡፡ ሀገራቸውን የሚያጠፉ እንደሆነ ገመቱ /መ.መሳ. 16÷1-3/፡፡ ጌታችንም በምድር ላይ ተመላልሶ በሚያስተምርበት ጊዜ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ሰዱቃውያን ሊይዙት ሊያጠምዱት አልቻሉም፡፡ ሲወድድ ይሰወርባቸዋል /ዮሐ. 12÷36/፡፡ አልያም ከመካከላቸው ተራምዶ ይወጣል /ዮሐ.10÷39/፡፡ የተንኮል ንግግራቸውን አውቆ መልስ እየሰጠ ይረታቸዋል /ሉቃ. 20÷1-2/፡፡ ከዚህም ምልክት የተነሣ ፈሩ፤ ተከዙና አዘኑም፡፡ «ዓለሙ ሁሉ እርሱን ተከትሎታል ሀገራችንንም የሮሜ ሰዎች ይወስዱታል» አሉ /ዮሐ. 12÷18/፡፡ ይህም ሶምሶን ለጌታችን ምሳሌ የሚሆንበት ሌላው የታሪኩ ክፍል ነው፡፡

ከዚያም ሶምሶን ወደ ሶሬቅ ሸለቆ ሔደ፡፡ ደሊላ የምትባልን አንድ ሴት ወደደ፡፡ ይህንንም ያዩ የፍልስጥኤማውያን ባላባቶች ወደ እርስዋ መጥተው የሶምሶንን ኃይል ምስጢር እንድታውቅላቸው ለመኑዋት፡፡ ብዙ ሰቅል የሆነ ብርንም ሊሰጥዋት ቃል ገቡ፡፡ እርሷም የሚወዳትን ሶምሶንን ለብር አሳልፋ እንደሸጠች ሁሉ ይሁዳም የሚወደውን ጌታውን ለሠላሳ ብር አሳልፎ ሸጧል፡፡ በዚህም ሶምሶን የጌታ፤ የፍልስጥኤማውያን ታላላቆች የአይሁድ ምሳሌ፤ ደሊላ ደግሞ የይሁዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

ደሊላም የሐሰት እንባ እያነባች ምስጢሩን ይነግራት ዘንድ አስጨነቀችው፡፡ መንፈሱም እስከ ሞት ድረስ ቃተተች፡፡ ሦስት ጊዜም ምስጢሩን እንዲነግራት ሞክራ በአራተኛው ተሳካ፡፡ ምስጢሩንም ለፍልስጥኤማውያን ነገረች፡፡ በዚህም የይሁዳ ምሳሌ ናት፡፡ ሶምሶን ደግሞ የጌታ ምሳሌ ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችንም በምሴተ ሐሙስ መንፈሱ እስከ ሞት ድረስ ከቃተተች በኋላ «ከእናንተ መካከል ዛሬ እኔን አሳልፎ የሚሰጠኝ አለ፤ እርሱም እጁን በወጪቱ ላይ የሚያጠልቀው ነው» አለ፡፡ ይሁዳም አይሁድ ሊይዙት በተደጋጋሚ ሞክረው ያቃታቸው መሆኑን ያውቃልና ሰዓቱ እንደ ቀረበ ሊሞትም እንዳለው የተናገረውን ምስጢር ሰምቶ ወደ አይሁድ ሄዶ «አሁንስ ኑና ተከተሉኝ በእጃችሁም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ» አለ /ሉቃ.22÷1-7፤ ዮሐ. 18÷6-7 ብሩን ተቀብሎ ጭፍሮቹን እየመራ ከመጣ በኋላ ጌታን የሚወድ መስሎ ቀርቦ ስሞታል፡፡

ሶምሶን ከእግዚአብሔር ጋር ወደ ተጣሉት አሕዛብ ፍቅር ስቦት ከደጋማው እስራኤል ምድር ወደ ቆላው የሶሬቅ ሸለቆ እንደወረደ ሁሉ፤ ጌታችንም ከእግዚአብሔር ጋር የተጣለው የአዳም ፍቅር ስቦት ከክብር ዙፋኑ ወደ ምድር ወርዶአል፡፡ ፍልስጥኤማውያኑም ሶምሶንን ከያዙት በኋላ ከሶሬቅ እስከ ጋዛ እያንገላቱ፣ እያዳፉ፣ እየጎተቱትም፣ ማየት ተስኖት ሲወድቅ ሲነሣ እየተዘባበቱበትና እየቀጠቀጡም ወሰዱት፡፡ ጌታችንንም የአዳም ፍቅር ስቦት ከእግዚአብሔር ጋር የተጣላውን የሰው ልጅ በመውደዱ ወደ ምድር ወርዶ እርሱ በሚወዳቸው በሰው ልጆች እጅ ከኢየሩሳሌም እስከ ቀራንዮ ድረስ ተንገላቷል፡፡ እያዳፉና በገመድ እየጎተቱ እየተዘባበቱበትም በመስቀል ላይ ሰቅለውታል፡፡

ከዚያም በኋላ ሶምሶን በመከራ ውስጥ በወኅኒ ቤት ሆኖ ወፍጮ በማስፈጨት እያሠቃዩት ኖረ፡፡ ጠጉሩም አደገለት፡፡ ፍልስጥኤማውያንም «ዳጎን» ሶምሶንን አሳልፎ በእጃችን ሰጠን ሲሉ ዳጎን ለተባለ ጣዖት ታላቅ በአል አደረጉለት፡፡ በአሉንም በግብር ቤት /በጥርብ ድንጋይ የተሠራ ግንብ/ ውስጥ ተድላ ደስታ አድርገው ደስ ሲላቸው «ሶምሶን ከእስር ወጥቶ ለኛ ዘፈን ይዝፈንልን፤ ይጫወትልን» ብለው ተናገሩ፡፡ በብላቴናም እየተመራ መጣ፡፡ ሶምሶንም ብላቴናውን የቤቱን ዋና ምሰሶዎች እንዲያሲዘው ለመነው፡፡ ብላቴናውም ወስዶ አስያዘው ከግንቡም በላይ ሶምሶን ሲዘፍን ሊያዩ የወጡ ብዙ ነበሩ፡፡ በቤቱም ውስጥ /በምድር ላይ/ የተቀመጡት የፍልስጥኤማውያን ባላባቶችም ስድስት መቶ ያህሉ ነበር፡፡

ጌታችንንም አይሁድ ከእስር ቤት አውጥተው «ስቀለው ስቀለው» እያሉ አስፈረዱበት፡፡ በመስቀልም ላይ በሰቀሉትም ጊዜ ተድላ ደስታ አደረጉ፡፡ «የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንክ ከመስቀል ላይ ውረድ፤ ብዙዎችን አዳነ ራሱን ግን ማዳን አይቻለውም» እያሉ ዘበቱ በዚያም ብዙ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን የአይሁድም ዋናዎች ነበሩ /ማቴ. 27÷22/፡፡ በዚህም ሶምሶን ለጌታችን ምሳሌ ይሆናል፡፡

ሶምሶን በግራና በቀኝ የነበሩትን ሁለቱን ምሰሶዎች ሲይዝ በሰውነቱ መስቀል ሠራ ቤቱንም ደግፈው የያዙትን ሁለቱንም ምሰሶዎች ያዘ፡፡ አምላካችንም በመስቀል ላይ ሆኖ ምዕራቡንና ምሥራቁን የዓለም ዳርቻ ያዘ፡፡ የሰው ልጆችን ሁሉ ሊያድን እንደወደደና ወደ እቅፉ ሊከተን ፈቃዱ እንደሆነ ሲያጠይቅ እጆቹን ዘርግቶ ዓለሙን ሁሉ ያዘ፡፡

ሶምሶንም ከምሰሶዎቹ መሀል ሆኖ «አምላኬ አንድ ጊዜ ብቻ እኔን አስበኝ» ብሎ ጸለየ /መ.መሳ. 16÷28/፡፡ አምላካችንም በመስቀል ላይ «ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ» አለ፡፡ ስለዚህም ሶምሶን አስቀድሞ የጮኸው ቃል ለጌታችን ምሳሌ ሆኗል፡፡

ሶምሶንም የቤቱን ዋና ምሰሶዎች በኃይል ገፋቸው፡፡ ቤቱም ተነዋወጸ፡፡ አራቱም ማዕዘን ተናጋ ከላይም ያለው ጥርብ ድንጋይ ሲወድቅ ከላይ የነበሩት ወደታች አብረው ወደቁ፡፡ ከሥርም ተቀምጠው በነበሩት ሁሉ ላይ ወረዱባቸው፡፡ የግድግዳውም ድንጋይ ተናደባቸው፡፡ ሶምሶንም ከፍልስጥኤማውያኑ ጋር አብሬ ልሙት ብሎ ጸልዮ ነበርና በዚያ ወደቀ፡፡ ነገር ግን በሕይወት ዘመኑ ከገደላቸው ጠላቶቹ ቁጥር ይልቅ በሞቱ ያጠፋቸው በዙ፡፡ ወንድሞቹና ዘመዶቹም ከፍርስራሹ ውስጥ አውጥተው በዞራና በኤሽታኦል ባለው ባባቱ መቃብር ቀበሩት፡፡

አምላካችንም በመስቀል ላይ ሆኖ ሳለ ሰይጣንን በነፋስ አውታር /ገመድ/ ወጥሮ በእሳት ዛንዥር /ሰንሰለት/ አስሮ ሲኦልን መዘበራት፡፡ ውስጥዋም ተናጋ፡፡ በሰማይም ላይ የነበሩት የአየር አጋንንት ወደ ሲኦል ወደቁ በምድር ላይ ያሉትንም አጠፋ፡፡ ጌታችን በዘመነ ሥጋዌው በምድር ተመላልሶ ከሰው እያወጣ ካጠፋቸው አጋንንት ይልቅ በሞቱ ያጠፋቸው በዝተዋል፡፡ በዚህም ሶምሶን የጌታችን ምሳሌ መሆኑን አንድምታው ወንጌል ያረጋግጣል /አንድምታ ማቴ. 2÷23/፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሶምሶን ለእናቱ አንድ እንደሆነ ተገልጧል /መ.መሳ. 13÷1/፡፡ እርሷም ሕይወቷን ሙሉ መካን ነበረች፡፡ ዘመዶቹ ግን ወንድሞቹ ተብለዋል፡፡ ጌታም ለእመቤታችን አንድያ ልጅዋ ነው፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 13÷56 ላይ ግን ዘመዶቹ እንደ አይሁድ ልማድ «ወንድሞቹና ቤተሰቦቹ» ተብለዋል፡፡ ስለዚህ ይህም ሶምሶንን ለጌታ ምሳሌ የሚያደርገው ሌላው ነገር ነው፡፡

በመጨረሻም ሶምሶን አንድም ሰው ከወገኖቹ ሳይረዳውና ሳያግዘው ብቻውን በጸጋ እግዚአብሔር የወገኖቹን ጠላቶቻቸውን ድል አድርጎ ነጻ እንዳ ወጣቸው ሁሉ፤ ጌታችንም ብቻውን ወደ ዓለም መጥቶ ወገኖቹ ከተባሉት እስራኤላውያን ማንም ሰው ሳይቀበለው መለኮቱን በሥጋ ገልጦ ከአጋንንት ባርነትና ከዘላለማዊ ሞት የሰው ልጆችን ነጻ አውጥቷል፡፡ በዚህም ሶምሶንን የእርሱ ምሳሌ እንዲሆን መድኃኒታችን እርሱ በኪነ ጥበቡ ዓለም ሳይፈጠር ገና በድንቅ አሠራሩ ወስኖት እንደነበር እንረዳለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ጽሑፉን ላደረሰችን ለእህታችን ለጽጌረዳ ይርጋ በእግዚአብሄር ስም እናመሰግናለን፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ቅዱስ ያሬድ ማነው? ከዳንኤል ክብረት

መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ፬ የሐዲስ ኪዳን መግቢያ

መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ፪