ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ጳውሎስ
ዲያቆን ታደሰ ወርቁ እነዚህ ሁለት ቅዱሳን አባቶቻችን የቅድስት ቤተክርስቲያናችን አዕማድ ናቸው፡፡ በመሠረትነት በአጸኗት ቤተክርስቲያን ያላቸው የክብር ሥፍራ ላቅ ያለ ነው፡፡ ይህ የሆነው እንዲሁ አይደለም፡፡ ለቤተክርስቲያንና በቤተክርስቲያን የፈጸሙት አገልግሎት በዚህም የተቀበሉት ሰማዕትነት ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ይህን መልካም የሆነውን ታሪካቸውን ለእኛ አርአያነት በሚሆን መልኩ ከትበውልናል፡፡ እኛም ለአርአርያነት በሚሆን መልኩ የእነዚህን ደጋግ ሁለት ቅዱሳን አባቶች ታሪክ፣ ዕውቀትና መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ከዚህ በመቀጠል አቅርበናል፡፡ 1. ሁለቱ ሐዋርያት ሲጠሩ የነበሩበት ሕይወት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በገሊላ ባሕር ዳር በምትገኘው በቤተ ሳይዳ ሲወለድ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ በጠርሴስ ከተማ ተወለደ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከወንድሙ ከእንድርያስ ጋር በገሊላ ባሕር ዓሣ ማሥገር ጀመረ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ በ 15 ዓመት ዕድሜው በገማልያ ትምህርት ቤት በመግባት የአይሁድን ሕግና ሥርዓት ተምሯል፡፡ በ30 ዓመቱም የአይሁድ ሸንጎ አባል ሆኗል፡፡ /1ቆሮ.1.17፤ሐዋ.22.3/