«ሐነጸ መቅደሶ በአርያም፤ መቅደሱን በአርያም /በልዕልና/ አነጸ»



በዲ/ በረከት አዝመራው

ሰኔ 20 እና 21 በእመቤታችን ስም በፊልጵስዩስ የታነጸችው የቤተክርስቲያን መታሰቢያ በዓል ነው፡፡ ይህች ሃገር ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ ተዘዋውረው ያስተማሩባትና ብዙ ምዕመናንን ያፈሩባት ቦታ ናት፡፡ ከዚያም በኋላ በዚህች ቦታ የመጀመሪያዋ በእመቤታችን ስም የታነጸች ቤተ ክርስቲያን መተከሏን የሰኔ 20 ስንክሳርና ሌሎችም ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡


የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን ምሥጢራዊ /mystical/ መልዕክቶች ከብዙ በጥቂቱ ማብራራት ነው፡፡ እያንዳንዱ ምዕመን እንደ ጥረቱና እንደ መንፈሳዊ እይታው ብዙ ድንቅ መልዕክቶችን ቢያገኝም ከብዙ ጥቂቱ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንና ማኅበረ ምዕመናን

በግእዝና በአማርኛው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «ቤተ ክርስቲያን» ተብሎ ተተርጉሞ የምናገኘው «አቅሌስያ» የሚለው የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙም «የኅሩያነ እግዚአብሔር የምዕምናን አንድነት» ማለት ነው፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህ ስም ከማኅበረ ምዕመናን በተጨማሪ ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያንም ይሰጣል፡፡ ይህም ሐዋርያዊ ትውፊት ነው፡፡ በሐዋርያት ዘመን ምዕምናን የሚገናኙበት ቤትም የምዕምናኑ አንድነትም «ቤተ ክርስቲያን» እየተባለ ይጠራ ነበር /ሮሜ 16.5 1ቆሮ. 11.8/፡፡ ዛሬም ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ትውፊት ጠብቃ ሕንፃውንም ማኅበረ ክርስቲያኑም «ቤተ ክርስቲያን» እያለች ትጠራለች፡፡

የቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ሕይወት ረቂቅና ምጡቅ፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚመረመር ሰማያዊ ነው፡፡ /1ኛቆሮ. 2.6-13/፡፡ ይህንን ረቂቅና ሰማያዊ ምሥጢር በተለያየ መንገድ ለትውልድ ማስተላለፍ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ጠንካራ ስራና መንፈሳዊ ጥበብ ይጠይቃል፡፡ አበው ይህን የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ከሚያስተላልፉበት መንገድ ዋነኛው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡

በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የሚገለጥ የቤተ ክርስቲያን ባሕርይ

1. የቤተ ክርስቲያን ሰማያዊና ምድራዊ ባሕርያት

በምድር ያለችው ቤተ ክርስቲያን ምድራዊም ሰማያዊም ገጽታ አላት፡፡ በአንድ በኩል ገና ጉዞዋን ያልጨረሰች፣ በምድር ላይ የሚኖሩና ለዚህም መብላት፣ መጠጣት የሚያስፈልጋቸው መድከም፣ መታመም. . .ያለባቸው አባላት ሕብረት ነች፡፡ ክርስቲያኖች ስቃይ፣ መከራ፣ ተጋድሎ የሚደርስባቸው በምድር ላይ እስካሉ ድረስ ነው፡፡ /ራዕ. 21.4/፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በምድር ያለች እግዚአብሔር መንግሥት የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ዕድገት እግዚአብሔር የሰውም ድርሻ አለበት፡፡ ሰዎች ይሰራሉ፤ እግዚአብሔር ስራቸውን ይባርካል፡፡ አገልጋዮች ሰዎች ሁሉ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ይደክማሉ፤ እግዚአብሔር ድካማቸውን አይቶ የሰዎችን ልብ ወደርሱ ይመልሳል፡፡ በአጠቃላይ ሰዎች ይጀምራሉ፤ እግዚአብሔር ይፈጽማል፡፡ ሰዎች ይተክላሉ እርሱ ያሳድጋል።

ነገር ግን በምድር የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከላይ የተጠቀሱትን ምድራዊ ሥራዎችን ይሰራሉ ማለት ሰማያውያን አይደሉም ማለት አይደለም፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያን በምድር ላይ በጉዞ ያለች በመሆኗ ምድራዊ ገጽታ ቢኖራትም እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ ጋር ባላት ኅብረት ደግሞ ሰማያዊት ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሥርዓተ አምልኮዎቿ /በቅዳሴዋ፣ በኅብረት ጸሎቶቿ. . ./ እንዲሁም እያንዳንዱ ምዕመን ባለው ሰማያዊ ሕይወት ምክንያት ከሰማያት ጋር ግንኙነት አላት፡፡ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ሕይወት በሰማያዊ ተስፋ የጸና እና የዚህን ምድር ኑሮ እንደመጻተኝነት የሚቆጥር ነው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «እኛ አገራችን በሰማይ ነውና ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስ እንጠባበቃለን፤ እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል፡፡» እንዲል /ፊል. 3.20/

እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ሁለት ባሕርያት በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ይገለጣሉ፡፡ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያነንን የሚሰሩት ሰዎች በመሆናቸው ሕንፃው የሰው ሥራ ቢሆንም፣ ቤተ ክርስቲያኑ ተሰርቶ በሜሮን ከከበረ በኋላ ግን እግዚአብሔር ቤት፣ ሰማያዊ መቅደስ፣ የመላዕክትና የቅዱሳን ቤት ይባላል እንጂ እንደተራ ቤት አይቆጠርም፡፡ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ቤተ ክርስቲያንን እና ነዋያተ ቅዱሳትን በቅብዓ ሜሮን ማክበር የማይቀር ሥርዓት ነው፤ ይህ ሥርዓት ቤቱ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰማያዊ ቤት፣ እግዚአብሔር የቅዱሳን ማደሪያ የሚሆንበት ነው፡፡ በአጠቃላይ በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሥራ ሰዎች ምድራዊ ቤት ይሰራሉ፤ እግዚአብሔር ሰማያዊ ያደርጋል፤ ሰዎች ባላቸው ጉልበትና ቁስ ቤት ሰርተው እግዚአብሔር ያስረክባሉ፤ እግዚአብሔር ደግሞ ደስ ይሰኙባት ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰማያዊት ቤት አድርጎ ይሰጣል፡፡ የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን መታነጽ በሚታሰብበት ዕለት /ሰኔ 20/ የሚዘመረው የቅዱስ ያሬድ ዜማም እንዲህ በማለት ይህንኑ ይገልጣል «ሐነጽዋ ለቤተ ክርስቲያን፤ ወሣረርዋ በመንፈስ ቅዱስ፤ ከመ ትኩን አርአያ ዘበሰማያት . . . ጊሡ ኀቤሃ፤ እስመ ኃይለ እግዚአብሔር ላዕሌሃ . . . ለዛቲ ቤተ ሣረራ አብ ቀዲሙ፣ ለዛቲ ቤት ሐነፃ ወልድ፤ ለዛቲ ቤት ወፈጸማ መንፈስ ቅዱስ. . . ሐነፀ መቅደሶ በአርያም፣ ቤተ ክርስቲያንን አነጿት /ገነቧት/ በሰማይ ላለችው አርአያ ትሆን ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ መሰረቷት. . . ወደርሷ ገስግሱ፤ እግዚአብሔር ኃይል በላይዋ ነውና . . . ያችን ቤት አብ አስቀድሞ መሠረታት፣ ያችን ቤት ወልድ አነፃት፣ ያችን ቤት መንፈስ ቅዱሰ ፈጸማት. . . መቅደሱን በልዕልና አነጸ»፡፡ ቅዱስ ያሬድ በመጀመሪያ. . . ሐነጽዋ ለቤተ ክርስቲያን. . . ቤተ ክርስቲያንን አነጿት ብሎ የሰዎችን ድርሻ ከገለጠ በኋላ ይህችን ቤት አብ መሠረታት፣. . . ወልድ አነፃት፣. . . መንፈስ ቅዱሰ ፈጸማት ብሎ፣ እግዚአብሔር ድርሻ ገለጸ።

ከላይ ባየነው መልኩ የቤተ ክርስቲያን ሰማያዊና ምድራዊ ገጽታ በሕንፃ ቤተ ክርስቲያንም ይንጸባረቃል፡፡ ስለዚህም ሁለቱም /ሕንፃው እና የምዕመናን ህብረት/ ምድራዊያን ስንላቸው ሰማያውያን፣ ሰማያውያን ስንላቸው ደግሞ በምድር ያሉ ናቸው፡፡

2. ድንጋዮች ተደራርበው የተሰራው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በምዕመናን አንድነት የተገነባች ቤተ ክርስቲያን ይገልጣል፡፡

ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ከድንጋይ መስራት የተለመደ ኦርቶዶክሳዊ ትውፊት ነው፡፡ ብዙ ድንጋይ በማይገኝባቸው የገጠር አካባቢዎች እንኳ ምዕመናን ከሌላ ቦታ አምጥተው በድንጋይ ያንፃሉ እንጂ በእንጨት ብቻ መስራት የተለመደ አይደለም፡፡ በድንጋይ መታነጹም ታላቅ ምሳሌያዊ ዋጋ ስላለው ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ምዕመናንን ሕያዋን ድንጋዮች፣ ጌታን የማዕዘን ራስ፣ ሐዋርያትና ነቢያትን መሰረት፣ ቤተ ክርስቲያንን /ማኅበረ ምዕመናንን/ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠራቸዋል፡፡ የመጀመሪዋ ቤተ ክርስቲያን በእመቤታችን ስም የታነጸችበት የመታሰቢያ በዓል ሲከበር በቅዳሴ ጊዜ የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት «እንግዲያውስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና እግዚአብሔር ቤተሰቦች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም፡፡ በሐዋርያና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፣ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በእርሱም ሕንፃ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ እግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ» በማለት ያብራራል፡፡ /ኤፌ. 2.19-22/ የዕለቱ የቅዱስ ጴጥሮስ መልዕክትም የሚነግረን ይህንኑ ነው «በሰውም ወደ ተጣለ እግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠና ክቡር ወደሆነው ወደ ሕያው ድንጋይ ወደ እርሱ እየቀረባችሁ እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መስዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንዲሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ» /1ኛጴጥ. 2.4-6/፡፡ ወንጌሉም «አንተ አለት ነህ በዚህም አለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን አንጻለሁ» በማለት ይህንኑ ምሥጢር ይገልጣል፡፡ /ማቴ. 16.13-19/፡፡

ኦርቶዶክሳውያን ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ በሩንም፣ ድንጋዩንም መሳማችን ትውፊታዊ ነው፡፡ ይህም አንዳንዶች እንደሚሉት ከየዋሕነትና ክብርን ለማይገባ የመስጠት ዝንባሌ ስላለን ነውን? አይደለም፤ በነዚሀ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አካላት ክርስቶስ አካል የሆነችዋን ቤተ ክርስቲያን /ክርስቶስ አንድ አካል የሆኑ ምዕመናን ሕብረት/ የምናይበት ውሰጣዊ አይን /በቅዱስ ኤፍሬም አገላለጽ ብሩህ አይን /luminous eye/ ስላለን ነው፡፡ ይህም ከመንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ ፀጋ ነው፡፡


3.
ቤተ ክርስቲያን ወደ መንግሥተ ሰማያት ጉዞ የምታደርግ መሆኗና መንግስተ ሰማያት በመካከላችን መሆኗ በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ይገለጣል፡፡


ቤተ ክርስቲያን በጉዞ ላይ ነች፡፡ በምድር ያለችው ቤተ ክርስቲያን በምድረ በዳ ሲጓዙ በነበሩት ሕዝበ እስራኤል ትመስላለች፡፡ ደብተራ ኦሪት ከምድረ በዳ ጀምራ ሰሎሞን በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እስከሰራበት ዘመን ድረስ በጉዞ ላይ ነበረች፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ጉዞዋን ጨርሳ እስክታርፍ ድረስ በጉዞ ላይ ነች፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ገልጦታል «እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፣ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፣ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ፡፡ እንዲህ የሚሉት ለእነርሱ የሚሆነውን አገር እንዲናፍቁ ያመለክታሉና፡፡ ያን የወጡበትን አገር አስበው ቢሆኑ ሊመለሱ ጊዜ በሆነላቸው ነበር፤ አሁን ግን የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፤ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና፡፡» /ዕብ. 11.13-16/ ፡፡

ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ወደ መንግሥተ ሰማያት የምትጓዝ ብቻ ሳይሆን መንግስተ ሰማያት በመካከሏ የሆነች /ሉቃ. 16.21/ እግዚአብሔር በምዕምናን መካከል የሚገኝባት የመንግሥተ ሰማያት አረቦን /ቀብድ/ ናት፡፡ የመንግሥተ ሰማያት ደስታዋና ሁሉም ነገሯ እግዚአብሔር በምዕመናን መካከል መገኘቱ ነው /ራዕ. 21.3-4/ በእያንዳንዱ ቅዳሴ፣ ጸሎት፣ የምዕመናን አንድነት ሁሉ እግዚአብሔር ይገኛልና /ማቴ. 28.19-20/ ቤተ ክርስቲያን የመንግስተ ሰማያት አረቦን ናት፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን «ሊመጣ ያለውን ዓለም ኃይል የቀመሱ» የሚላቸው /ዕብ. 6.5/

እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ሁለት ገጽታዎች በሕንፃው ይገለጣሉ፡፡ በኦርቶዶክሳውያን ትውፊት በቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ አውልጥቶ /with west to east orientation/ ይሰራል፡፡ ይህም የቤተ ክርስቲያንን «ምሥራቃዊ ጉዞ» ያመለክታል፤ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዓለም ባህር ወደ ምሥራቅ /ወደ መንግስተ ሰማያት/ የምትቀዝፍ መርከብ ናት /1ኛጴጥ. 3.20/፡፡ ይህም የገነት ምሳሌ ነው «እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔደን ገነትን ተከለ፤ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው» እንዲል /ዘፍ. 2.8/፡፡ ነገር ግን ወደ ምሥራቅ ስንዞር ፊት ለፊት የምናገኘው መሰዊያውን ነው፡፡ በእውነትም ቤተ ክርሰቲያን ከዕፀ ሕይወት /በመሰዊያው ላይ ካለው የጌታ ስጋና ደም/ የምንበላባት የደስታ ገነታችን ናት፡፡ ስለዚህ ወደ ምስራቅ መዞራችን የጉዟችን አቅጣጫ ሲያመለክት መሰዊያው በመካከላችን መሆኑ ደግሞ መድረሻችን ቀብድ ሆና በመካከላችን መገኘቷን ያመለክታል፡፡

4.
ቤተ ክርስቲያን የዓለም ብርሃን መሆኗ በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ተገልጧል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ብርሃን እግዚአብሔር ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አምሳል ስለሆነችው ኢየሩሳሌም ሰማያዊት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል «ለከተማይቱ እግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት፣ መብራትዋም በጉ ስለሆነ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጋትም ነበር፡፡ አሕዛብም በብርሃኗ ይመላለሳሉ፡፡ /ራዕ. 21.23/ ነቢዩ ኢሳይያስም አስቀድሞ በትንቢቱ «ብርሃንሽ መጥቷልና፣ እግዚአብሔር ክብር ወጥቶልሻልና ተነሽ አብሪ፡፡ እነሆ ጨለማ ምድርን፣ ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይወጣል፤ ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ ነገሥታም ወደ መውጫሽ ፀዳል ይመጣሉ» ብሎ ስለ ቤተ ክርስቲያን /ጽዮን/ ተናግሯል፡፡ /ኢሳ. 60.1/ ይህን እግዚአብሔር ብርሃን ተቀብላ ብርሃን የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የዓለም ብርሃን /ማቴ 524/

ይህ የቤተ ክርስቲያን ብርሃንነት በሕንፃዋ ይገለጣል፡፡ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ከውጭ ወደ ውስጥ ለሚገባ ብርሃን ብዙም ትኩረት አይሰጥም፡፡ ይህም የጸሐይ ብርሃን ተጠልቶ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ብርሃን እንደሆነችና ከጨለማው ዓለምም ብርሃንን እንደማትፈልግ ለማመልከት ነው። ኦርቶዶክሳዊው ትውፊት በጧፍና በመብራት /በቀንዲል/ ቤተ ክርስቲያንን በብርሃን ማስጌጥ ነው፡፡ ቀንዲል በዘይት የሚበራ መብራት ነው፡፡ ዘይት የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው /1ኛዮሐ. 2.27/፡፡ ይህም ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ በክርስቲያኖች ላይ የሚያበራ የልቦና ብርሃንን ያመለከታል። ይህ የልቦና ብርሃንም እግዚአብሔር የማወቅ፣ ሰማያዊውን እግዚአብሔር ክብር በልቦና የማየት፣ በአጠቃላይ በጨለማው ዓለም ውስጥ ከብርሃን አምላክ እግዚአብሔር ጋር መኖር ነው፤ እግዚአብሔር ብርሃን ነውና፡፡ ይህንን ምሥጢር በዚህ በዓል /ሕንጸታ ቤተ ክርስቲያን/ የሚዘመረው የቅዱስ ያሬድ ዜማ እንዲህ ይገልጠዋል «ሐነጽዋ ለቤተ ክርስቲያን፤ ወሣረርዋ በመንፈስ ቅዱስ፤ ከመ ትኩን አርአያ ዘበሰማያት. . . ትበርህ እምከዋክብት. . . በጽድቁ ሐወፃ፤ እምነ ጸሐይ ይበርህ ገጻ፣ ቤተ ክርስቲያንን አነጿት፤ በመንፈስ ቅዱስም መሠረቷት፤ በሰማይ ላለችው አርአያ ትሆን ዘንድ. . . ከከዋክብት ይልቅ ታበራለች. . . በጽድቁ ጎብኝቷታል፤ ከጸሐይ ይልቅ ፊት ይበራል፡፡» በሌላም በተለያዩ ቦታዎች ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያንን «ትበርህ ከመ ኮከበ ጽባሕ፤ ወታስተርኢ ከመ ጎሕ፤ ንቁሐነ ንኩን ትጉሃነ ንጊሣ ለቤተ ክርስቲያን፤ እንደ ማለዳ ኮከብ ታበራለች፤ እንደ ጎሕም ትታያለች፤ ንቁዎች እንሁን፣ ተግተን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንገስግስ» ይላል፡፡

5.
መስቀል ወደ ሰማይ የወጣንበት መሰላል መሆኑ በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ተገልጧል፡፡

የጌታ መስቀል ሰማይና ምድር የታሩቁበት፣ ምድራዊያን ወደ ሰማያት የደረሱበት መሰላል ነው፡፡ ይህንም ጌታ እንዲህ ብሎ ገልጦታል «ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ፡፡» /ዮሐ. 12.32/ ጌታ ከፍ ከፍ ባልኩ ጊዜ ማለቱ በመስቀል ላይ በወጣሁ ጊዜ ለማለት ነው፤ ሁሉን በፍቅሩ የሳበበት፣ ሞትን የሻረበት፣ ገነትን የከፈተበት፣ በአጠቃላይ ሰማይና ምድርን ያስታረቀው በመስቀሉ ነውና፡፡ በዚህ በዓል የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክትም «እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግርግዳ በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ፣ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፣ ጥልን በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል እግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፡፡ መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፣ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምሥራች ብሎ ሰበከ፤ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና፡፡ እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና እግዚአብሔር ቤተሰቦች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም፡፡» ይላል /ኤፌ. 3.19/፡፡ በአጠቃላይ በጌታ መስቀል እግዚአብሔር ሰው ታርቀዋል፤ እግዚአብሔር መላዕክቱ በሰዎች መካከል የሚገኙ ሆነዋል፤ ሰዎችም በምድር እንኳ ሆነው ልቦናቸው በሰማይ መኖር የሚችል ሆኗል፡፡

ይህ የመስቀል ምሥጢር በሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የተገለጠ ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ትውፊት ቤተ ክርስቲያን ከጉልላቷ ጀመራ እስከ አጥር ቅጥሯ ድረስ በመስቀል ያጌጠች ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሰማያውያንና ምድራውያን የሚገናኙባት እግዚአብሔር ቤት ናት ካልን፣ ይህን ያገኘችው ክርስቶስ መስቀል ነው፡፡ መስቀል የመንግሥተ ሰማያት መለኮታዊ አርማ ነው፡፡ ስለዚህ በሰማያት ላለችው ለኢየሩሳሌም አምሳል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን መስቀል አርማዋ፣ መለያዋ ነው፡፡ ስለዚህም የመስቀል፣ የቤተ ክርስቲያንና የመንግሥተ ሰማያት ምሥጢር የተሰናሰለ ነው፡፡

በሌላም በኩል መስቀል የቤተ ክርስቲያን ኃይሏና ግርማዋ ነው፤ ቅዱስ ጳውሎስ «የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን እግዚአብሔር ኃይል ነውና» እንዳለ፡፡ /1ቆሮ. 1.18/ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንም በመስቀል ማጌጡ ኃይልንና ግርማን እንዲለብስ ያደርገዋል፡፡ ይህንንም ቅዱስ ያሬድ በዕለቱ ዜማው «ጊሡ ሃቤሃ፤ እስመ ኃይለ እግዚአብሔር ላዕሌሃ፤ ወደርሷ ገስግሱ፤ እግዚአብሔር ኃይል በላይዋ ነውና» በማለት ገልጾታል፡፡

በአጠቃላይ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የቤተክርስቲያንን ባሕርይ የሚያንጸባረቁ ብዙ ምሥጢራት ያሉት እንጂ በዘፈቀደ የሚሰራ አይደለም፡፡ በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን የሚያንጹ ሰዎችም /ባለሙያዎች/ የቤተ ክርስቲያን አሠራር ትውፊታዊ ዕውቀት ያላቸው፣ እነርሱም ራሳቸው የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች የሆኑ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ቢሆኑ አባቶቻችን በዚህ መልኩ በትውፊት እንዲተላለፍ ያስቀመጡት መንፈሳዊ መልዕክት ተጠብቆ ለትውልድ ይተላለፋል፡፡

ይህም ደብተራ ኦሪትን ይሠራ ዘንድ እግዚአብሔር በመረጠው ሰው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ሰው እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲህ ብሏልና «እይ ፤ከአይሁድ ነገድ የሚሆን የሆር የልጅ ልጅ፣ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ፡፡ በሥራ ሁሉ ብልሃት፣ በጥበብም፣ በማስተዋልም በዕውቀትም እግዚአብሔር መንፈስ ሞላሁበት፤ የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ. . .» /ዘጸ. 31.1-4/፡፡

አምላከ ቤተ ክርስቲያን አይለየን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ጽሁፉን ላደረሰችን ለጽጌረዳ ይርጋ በእግዚአብሔር ስም ምስጋናችን ከልብ ነው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ቅዱስ ያሬድ ማነው? ከዳንኤል ክብረት

መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ፬ የሐዲስ ኪዳን መግቢያ

መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ፪