‹‹ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና፡፡›› ማቴ 5፥10
በዲ/ን አሉላ መብራቱ
ስደት፡- በቁሙ መስደድ ፣መሰደድ ፣መለየት፣ ቦታን መልቀቅ፣ ከሀገር ከዘመድ መራቅ፣ መፍለስ፣ መነቀል ማለት ነው፡፡
ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ የተባሉት እውነትንና ጽድቅን ለማወቅ ወይም ለማስተማር ወይም በምናኔ ምክንያት ሀገራቸውን ጥለው የተሰደዱ፣ እውነትን በመናገራቸው ስለ እውነተኛይቱ ሃይማኖት በመቆማቸው፣ በእግዚአብሔርና በምዕመናን ፊት ሞገስንና መወደድን በማግኘታቸው ምክንያት በመናፍቃን፣ የራሳቸውን ክብር በሚፈልጉ ቀናተኞች ወይም በአላውያን ነገሥታት የተሰደዱትን ነፍሳቸውንና ሥጋቸውን ሊያጠፉ ከተነሱት አካላት የሸሹትን፣ ከምንፍቅናና ከስህተት አስተሳሰቦች ራሳቸውን የለዩና ያሸሹትን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡
በዚህች ጽሑፍ ስለ እውነት በመቆማቸው፣ የእውነተኛይቱ ሃይማኖት ጠበቃ በመሆናቸው ምክንያት ሊገድሏቸውና ሊያጠፏአቸው ከሚፈልጉ መናፍቃንና ምድራዊ ክብርን ከሚፈልጉ ቀናተኞች ስለሚሸሹ እውነተኞች ክርስቲያኖች እንመለከታለን፡፡
ስለምን መሰደድ ያስፈልጋል? (የስደት ዓላማው ምንድን ነው?)
1. ለእያንዳንዱ ሰው የተወሰነ ጊዜና ሰዓት አለው
ለክረምትና ለበጋ፣ ለሀጋይና ለፀደይ ጊዜ እንዳላቸው ሁሉ ለእያንዳንዱ ሰው ለመኖርም ሆነ ለመሞት የተወሰነለት ጊዜ አለው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ለመወለድ ጊዜ አለው ለመሞትም ጊዜ አለው፡፡›› እንዳለ፡፡(መክ 3፥2)
ጌታችን የእኛን ሥጋ የተዋሐደና ከኃጢአት በቀር የሰውን ድካም የገለጠ ስለሆነ እንደሰውነቱ የሠራቸውን ሥራዎች ሁሉ እንድናደርግ ምሳሌውን ትቶልናል፡፡ ቅዱስ አትናቴዮስ እንዳለ እርሱ(ጌታችን) እግዚአብሔር እንደመሆኑ መጠን ለርሱ ጊዜ የሌለውና ጊዜንም የፈጠረ ራሱ ሲሆን ሰው ሆኖ እያንዳንዱ ሰው የተወሰነለት ጊዜ እንዳለው አስተማረን፡፡ ስለዚህም ‹‹ሊይዙት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አልጫነበትም›› ተባለለት፡፡ (ዮሐ 7፥30) ራሱም ‹‹ጊዜዬ ገና አልደረሰም፡፡›› ብሎ ተናገረ፡፡ (ዮሐ 7፥6) (ዮሐ 2፥4) እደገናም ጊዜው በደረሰ ጊዜ ‹‹እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፣ እነሆ ሰዓቲቱ ቀርባለች፣ የሰው ልጅም በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል›› ብሎ ተናገረ፡፡(ዮሐ 26፥45)
ይህ ለእያንዳንዱ ሰው ለመኖርም ለመሞትም የተወሰነለት ጊዜና እንዴት እንደተወሰነለት ለማንም ሰው የማይታወቅና የተሰወረ ነው፡፡ ይህም ነገር ከቅዱሳን አነጋገር በግልጽ ታውቋል፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹የዘመኔን አነስተኛነት ንገረኝ›› በማለት የማያውቀውን ነገር ያውቅ ዘንድ ጠየቀ በሉቃስ 12፥20 ላይ የተጠቀሰው ባለጸጋ ብዙ ዘመን እኖራለሁ ብሎ ሲያስብ ‹‹አንተ ሰነፍ፣ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዷት ይፈልጓታል፣ ይህ ያከማቸኸው ለማን ይሆናል?›› ተባለ፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ‹‹ሰውም ጊዜውን አያውቅም›› አለ፡፡ (መክ 9፥12) ይስሐቅም ለልጁ ለኤሳው ‹‹እኔ አረጀሁ፣ የምሞትበትን ቀን አላውቅም›› አለ፡፡ (ዘፍ 27፥2)
እውነተኛው መምህር መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ክርስቲያኖች ጊዜያቸው ሳይደርስ ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው እንዳይሰጡ በቃልም በተግባርም አስተማረ፡፡ በቃል ‹‹በአንዲቱ ከተማ መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ›› እንዲሁም ‹‹በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰችው ሥፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል፤ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፣ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ፡፡›› ሲል አስተማረ፡፡ (ማቴ 10፥23፣ ማቴ 24፥15-18) በተግባር ደግሞ ገና ትንሽ ሕፃን ሳለ ሄሮድስ ሊገድለው በፈለገ ጊዜ በራሱ መልአክ ዮሴፍን ‹‹ተነሣ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ ሄሮድስ ሕጻኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና›› ብሎ አዘዘው፡፡ (ማቴ 2.፥13) ወደ ግብጽም ተሰደደ፡፡ ሄሮድስ ሲሞት ደግሞ በአባቱ ፋንታ የነገሠውን ልጁን አርኬላዎስን ከመፍራት የተነሣ ወደ ናዝሬት ሔደ፡፡ (ሉቃ 2፥51) ኋላም አምላክነቱን በሥራው እየገለጠ ሲመጣ ህሙማንን በመፈወሱ፣ እንደነ አልዓዛር ያሉ ሙታንን በማስነሳቱ አይሁድ በቅናት ሊገድሉት በፈለጉ ጊዜ የሰውን ልጅ ሊያድንበት የቆረጠው ጊዜ አልደረሰምና ራሱን አሳልፎ አልሰጠም፡፡
ቅዱሳን ከመድኃኒታቸው ከኢየሱስ ክርስቶስ በመማር ሁሉን በአግባቡ አደረጉ፡፡ የመሞት ጊዜያቸውን ሳያሳውቃቸው ሊገድሏቸው ለሚፈልጉ ጠላቶቻቸው እጃቸውን አልሰጡም፡፡ ከጌታችን መገለጥ በፊት የነበሩ ቅዱሳን ነቢያት በጌታ ትምህርት ውስጥ ነበሩና ከአሳዳጆቻቸው ሸሹ፤ ቅዱስ ጳውሎስም ስለ እነርሱ ሲናገር ‹‹ሁሉን እያጡና መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፣…… በምድረ በዳና በተራራ፣ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ›› አለ፡፡ (ዕብ 11፥37-38) ነቢዩ ኤልያስ ኤልዛቤል ‹‹ነፍስህን ከእነዚህ እንደ አንዲቱ ነፍስ ባላደርጋት…..›› ብላ መልእክት በላከችበት ጊዜ ነፍሱን ሊያድን ሸሸ፡፡ (1ኛ ነገ 19፥2-3) የጌታ ደቀመዛሙርት አይሁድን ከመፍራታቸው የተነሣ ራሳቸውን ደብቀዋል፤ ቅዱስ ጳውሎስም የደማስቆ ገዢ በፈለገው ጊዜ በቅጥሩ ባለ መስኮት በቅርጫት አውርደውት ከእጁ አምልጧል፡፡ (2ኛ ቆሮ 11፥32)
ስለዚህ ክርስቲያኖች ሁሉ ሰው እንደመሆናቸው ፈቃደ እግዚአብሔር የወሰነላቸውን ጊዜ ስለማያውቁ ሊገድሏቸውና ሊያጠፏቸው ከሚሸምቁባቸው ይሸሻሉ፤ ይሰደዳሉ፡፡
2. እግዚአብሔርን መፈታተን አይገባም
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእያንዳንዱ ሰው የተወሰነለት ጊዜ እንዳለው እንዳስተማረን ሁሉ ክርስቲያኖች ‹‹እግዚአብሔር ያድነኛል፣ እግዚአብሔር ይረዳኛል፡፡›› ብለው ወደ ፈተና ራሳቸውን እንዳይከቱ አስተምሮናል፡፡ በሊቀ ነቢያት ሙሴ አድሮ ‹‹አምላካችሁን እግዚአብሔርን አትፈታተኑት›› አለን፡፡ (ዘዳ 6፥16) በዮርዳኖስ ከተጠመቀ በኋላ ‹‹ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ ራሱ ሄደ አልተባለም፡፡(ማቴ 4፥1) ሐዋርያትን ሲያስተምር ‹‹ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ›› አለ፡፡ (ማቴ 26፥41) በታላቁ ጸሎትም ‹‹ወደ ፈተና አታግባን›› ብለን እንድንጸልይ አስተማረን፡፡ (ማቴ 6፥13) ራሱም ለሞት ተላልፎ የሚሰጥበት ጊዜ ሲቀርብ ምንም እንኳ አስቀድሞ ሊያድነን የወሰነና ከአባቱ ጋር በፈቃድ አንድ ቢሆንም በፈተና ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚገባን ሊያስተምረን ‹‹አባቴ ቢቻልስ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን፡፡›› አለ፡፡ (ማቴ 26፥39) በዚህም ቅዱሳን ራሳቸውን ወደ ፈተና እንዳያስገቡ ፈተናው የግድ ከሆነ ደግሞ ፈቃዳቸውን ለእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲያስገዙ አስተማረ፡፡ ዳግመኛም በገዳመ ቆሮንቶስ ዲያብሎስ ‹‹የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ወደታች ራስህን ወርውር፡፡›› ባለው ጊዜ ‹‹ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል›› አለው፡፡ (ማቴ 4፥6-7) ዲያብሎስ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ›› የሚለውን ቀንሶ የተቀረውን በመጥቀስ ጌታን ‹‹ራስህን ወርውር›› አለው ቅዱሳን ‹‹በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ›› ተባለላቸው፤ መንገዳቸው ሁሉ በፈቃደ እግዚአብሔር የሚመራ ነውና፡፡ ፈተናን የሚያመጣ፣ ክርስቲያኖችን የሚያሳድድ ነፍሰ ገዳይ ፣ወርውሮ ለመጣል የሚሞክር ዲያብሎስ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ ራስን ለአሳዳጅ አሳልፎ መስጠት ከዲያብሎስ ጋር መተባበር እግዚአብሔርን መፈታተን ነው፡፡ ስለዚህ ጌታችን ‹‹ጌታን አምላክህን አትፈታተነው›› ብሎ አሳፈረው፡፡
ቅዱሳን የመድኃኒታቸውን አርአያ ተከትለው መንፈስ ቅዱስ ካልመራቸውና ካላመለከታቸው በስተቀር ያለ አግባብ ራሳቸውን አሳልፈው እንዳይሰጡ ይህም ራሳቸው መግደልና በዚህም የነፍስ ገዳይነት ወንጀል ተሸካሚዎችና የዲያብሎስ ተባባሪዎች እንዳይሆኑ ይጸልያሉ፤ ከጠላቶቻቸውና ከአሳዳጆቻቸው ይሸሻሉ ይሰደዳሉ፡፡
3. ስደት ለእግዚአብሔር ፈቃድ መታዘዝ እንጂ ፍርሃት አይደለም
ከላይ እንደተመለከትነው ቅዱሳን ሊገድሏቸው ለሚፈልጉ ራሳቸውን ያለአግባብ አሳልፈው አልሰጡም፡፡ ይህንንም ያደረጉት ሞትን ከመፍራት ሳይሆን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ለመታዘዝ ነው፡፡ ጌታችንም ሊገድሉት ከፈለጉት ከሄሮድስ እና ከቀናተኞች አይሁድ ራሱን ሰወረ፤ ለመስቀል ሞት የቀጠረው ጊዜ ገና ነበርና፡፡ ይህ ግን ፍርሃት አልነበረም፡፡ ይህም የሚታወቀው ስለ ቤዛ ብዙኃን መከራ ይቀበል ዘንድ የቆረጠው ጊዜ ሲደርስ ለአባቱ ‹‹አባት ሆይ ሰዓቱ ደርሶአል፣ ልጅህን አክብረው፡፡›› በማለቱ ነው፡፡ (ዮሐ 17፥2) ሊይዙት ከሚፈልጉትም ራሱን አልደበቀም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሊይዙት ወደ እርሱ የመጡትን ‹‹ማንን ትፈልጋላችሁ?›› እንዳላቸውና እነርሱም ‹‹የናዝሬቱን ኢየሱስ?›› ባሉ ጊዜ ‹‹የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ›› እንዳላቸው ይነግረናል፡፡(ዮሐ 18፥4-5)
ቅዱሳንም ይህን በማድረጋቸው ፈሪዎች ሳይሆኑ በእውነት ጽኑዓንና ጀግኖች መሆናቸው ታውቋል፡፡ ቀድሞ ራሱን ከኤልዛቤል ደብቆ የነበረው ቃላቁ ኤልያስ አክአብን እንዲያገኝና አካዝያስን እንዲገስጽ በመንፈስ ቅዱስ በታዘዘ ጊዜ አልፈራም፡፡ (1ኛ ነገ 20፥17) አይሁድን በመፍራት ተደብቆ የነበረው ቅዱስ ጴጥሮስና በቅርጫት የወጣውና ያመለጠው ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹በሮም ትመሰክሩልኝ ዘንድ ይገባችኋል፡፡›› በተባሉ ጊዜ ደስ እያላቸው ሔዱ፤ (Euseb.Hist. Eccl 2:25) አንዱ ወዳጆቹን ሊገናኝ እየቸኮለ እንደሚሄድ ሰው ሆኖ ሞቱን በደስታ ተቀበል፤ ሌላውም ጊዜው ሲደርስ ‹‹የምሔድበትም ጊዜ ደርሷል›› እያለ በሞቱ ደስ ተሰኘበት፡፡(2ኛ ጢሞ 4፥7) ከቅዱሳን አንዳንዶች ራሳቸውን ለአሳዳጆቻቸው አሳልፈው የሰጡ አሉ፡፡ ይህንንም ያደረጉት ያለምክንያት አይደለም፤በውስጣቸው የተሸከሙት መንፈስ ቅዱስ ስላነሳሳቸው እንጂ። በ107 ዓ.ም ገደማ የአንጾኪያ ሊቀጳጳስ የነበረው ቅዱስ አግናጥዮስ በሊቀ ጳጳስነቱና በክርስትና ሃይማኖቱ ጠንካራ አቋም ምክንያት ተይዞ በአላዊው ንጉሥ ትራጃን ‹‹በውስጡ ያን የተሰቀለውን መሸከሙን ያረጋገጠው አግናጥዮስ በወታደሮች ታስሮ ወደ ታላቋ ሮም በመሄድ እዚያም ለሕዝቡ መደሰቻ በአራዊት እንዲበላ አዘናል፡፡›› በሚል ትዕዛዝ ታስሮ በነበረበት ጊዜ ለሮም ክርስቲያኖች ‹‹ይህንን በምጽፍላችሁ ጊዜ ምንም እንኳ በሕይወት ያለው ብሆንም ለመሞት እጅግ ጓጉቻለሁ፡፡ ፍቅሬ(የዚህ ዓለም) ተሰቅሏል(ጠፍቷል)፤ ልብላ ልብላ የሚያሰኝ የምኞት እሳት በውስጤ የለም፤ ነገር ግን በእኔ ያለ ህያውና ነባቢ(የሚናገር) ውሃ (መንፈስ ቅዱስ) ወደ አብ ና እያለ ይጠራኛል፡፡›› የሚል መልእክት ጽፎላቸው ነበር፡፡ ወዲያውም በአናብስት ተበልቶ ሰማዕትነትን ተቀብሏል፡፡ እንዲህ ያሉ ቅዱሳን ራሳቸውን አሳልፈው እንደሰጡ ወዲያው በሰማዕትነት ተገድለዋል፣ ቅዱስ አትናቴዎስ እንዳለ የድፍረታቸውና ራሳቸውን ለጠላቶቻቸው አሳልፈው የመስጠታቸው ነገር ከመንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ታወቀ፡፡
4. ቅዱሳን ክፋትን ለመቀነስ ይሰደዳሉ።
በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠረን የሰው ልጅ ነፍስ ማጥፋት ታላቅ ክፋት፣ ታላቅ በደል ነው፡፡ ይህንንም ጌታችን ‹‹እናንተ ግብዞች ጸፎችና ፈሪሳውያን የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ፣ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና ‹በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር ስለምትሉ ወዮላችሁ፡፡ እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ፡፡ እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ሙሉ ፤እናንተ እባቦች የእፉኝት ልጆች፣ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ? ስለዚህ እነሆ ነቢያትንና ጥበበኞችን ፃፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ፤ ትሰቅሉማላችሁ፤ ከእነርሱም በምኩራባችሁ ትገርፋላችሁ፤ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሰዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ፡፡›› በማለቱ እንረዳለን፡፡ (ማቴ 23፥29-36)
በቅዱሳን ደም መጠየቅ እንዴት ያስፈራል? ጌታችን ‹‹ወዮላችሁ››፣‹‹እናንተ እባቦች፣ የእፋኝት ልጆች››፣ ‹‹ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?›› ‹‹በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ›› በማለቱ የበደሉን ታላቅነት ፤ የቅጣቱንም አስከፊነት አመልክቷል፡፡ ወንድሙን ከገደለው ቃየል ሳይማር በነፍሰ ገዳይነት የተገኘው ላሜሕ ‹‹እኔ ጎልማሳውን ለቁስሌ ብላቴናውንም ለመወጋቴ ገድዬዋለሁና ቃየልን ሰባት እጥፍ ይበቀሉታል፤ ላሜሕን ግን ሰባ ሰባት እጥፍ›› ብሏል፡፡ (ዘፍ 4፥24)
ስለዚህ ቅዱሳን ዲያብሎስ በልቡናቸው አድሮ በቅናት ተነሣስተው ሊገድሏቸው ከሚፈልጉ ሰዎች ክፋትንና ነፍሰ ገዳይነትን ለመቀነስ ስለጠላቶቻቸው አስበው ይሰደዳሉ፡፡
ስደትን እንዴት ሊቀበሉት(ሊኖሩት) ይገባል?
-; ያለመማረር በትዕግስት
የሞተ ሰው ስቃዩ ያበቃል፤ የሸሸ ግን የጠላቶቹን አደጋ ጣይነት በየቀኑ ሲያስብ ሞት ቀላል ሆኖ ይታየዋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሁሉን እያጡና መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፣……. በምድረ በዳና በተራራ፣ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ›› እንዳለ ቅዱሳን አስቸጋሪና ፈታኝ የሆነውን የስደት ጊዜ በትዕግስት አሳለፉት፤ በመስቀል ጉዞ መከራው ከባድ ቢሆንም ከእግዚአብሔር የሆነ ሰላምና ደስታ አለና፡፡ ራሱ መከራ የተቀበለ ቅዱስ ዳዊትም መከራ የሚቀበሉትን እንዲህ በሚሉ ቃላት ያጽናናቸዋል ‹‹በእግዚአብሔር የምታምኑ ሁላችሁ ታገሡ፣ ልባችሁንም አጽኑ›› (መዝ 20፥24) ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ፈተና ሊጎበኙ ታገሱ ያሉትን ሁሉ ‹‹በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግስት ሊያሳልፉት ይገባል፡፡
; ስደት የእውነተኛ ሰዎች(ክርስቲያኖች) መገለጫ እንጂ ጥቂት ሰዎች ላይ ብቻ የሚደርስ አይደለም፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስን በማምለክ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ›› እንዳለ ስደት የክርስቲያኖች መገለጫ ነው፡፡ አባታችን ኢዮብም ‹‹በምድር ላይ የሰው ሕይወቱ ብርቱ ሰልፍ አይደለምን»? አለ፡፡ (ኢዮ 7፥1) ጌታችንም ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባቸው፤ ነገር ግን አይዞአችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ፡፡›› ብሎ አስተማረን ፡፡የስደቱ ዓይነት ግን ይለያያል።አንዳንዶች በአካል ሲሰደዱ ሌሎቹ በኅሊና ይሰደዳሉ።ዓለም እንደሚያስበው አለማሰብና ከዓለም የውሸት አሉባልታ መለየት የኅሊና ስደት ነው።እንደዚህ ያሉትን ክርሰቲያኖች በእውነት ዓለም በኅሊና ያሰድዳቸዋል።
ስለዚህ ስደት የክርስቲያኖች ሕይወት መሆኑን በማሰብ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በደስታ ሊያሳልፉት ይገባል፡፡
; ሓላፊነትን በመወጣት
ቅዱሳን የሽሽታቸውን ጊዜ በከንቱ አላሳለፉም፣ ሲሳደዱም ከፍርሃት የተነሣ የሌሎችን ደኅንነት አልዘነጉም፤ የእውነትን ቃል በየደረሱበት ለሁሉም ሰው ማካፈልን ችላ አላሉም፡፡
በቅዱስ እስጢፋኖስ ሰማዕትነት ምክንያት ‹‹በኢየሩሳሌም ባለች ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ሆነ››። የተበተኑትም ጊዜያቸውን ያለ ሥራ አላሳለፋም፡፡ በሄዱበት ሁሉ ወንጌልን ሰበኩ፡፡ ስለዚህም ‹‹የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ፡፡›› ተባለላቸው፡፡ (ሐዋ 8፥4) ቅዱስ አትናቴዎስ አርዮሳውያን ባሳደዱት ጊዜ ያለ ሥራ አልተቀመጠም፡፡ ስለ በጎቹ ሕይወትና ስለ አሳዳጆቹ እንቅስቃሴ በጥንቃቄ ይከታተል ነበር፡፡ ለአሳዳጆቹም ወሬ ተገቢውን መልስ ሰጥቷል፡፡ ምዕመናንን በትምህርቱ ከመምከርና ከመንከባከብ አልቦዘነም፡፡ ስለዚህም ቅዱሳን በዚህ ወቅት ሓላፊነትን በአግባቡ መወጣት፣ ይልቁንም በጾምና በጸሎት መትጋት እንደሚገባ ከሌሎች ጊዜያት በበለጠ በጽኑ ትኅርምትና ተጋድሎ ውስጥ በመሆን አስተማሩን፡፡
በስደት ወቅት የሚገኙ በረከቶች
; እግዚአብሔር ለቅዱሳን ታላላቅ ነገሮችን ያደረገው በስደታቸው ወቅት ነው፡፡
ስደት ከፍተኛ የሆነ መከራና ፈተና ያለበት በመሆኑ ሰዎች የክርስትናን የሕይወት መመሪያዎች የሚቀስሙበት ትምህርት ቤት ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ አስቀድሞ ከፈርኦን ቤት በቀሰመው እውቀትና በኃይሉ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ነጻ እንደሚያወጣ ያስብ ነበር፡፡ በስደት ሆኖ መንፈሳዊውን እውቀት ከቀሰመ በኋላ ግን ‹‹ወደ ፈርዖን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብጽ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?›› አለ፡፡ በዚህም የእግዚአብሔርን ጸጋ ለመቀበል የበቃ ሆነ፤ ታላቁንም ራዕይ አየ፡፡ እግዚአብሔር ላደረጋቸው ለእነዚያ ድንቅ ድንቅ ለሆኑ ተአምራትና ለተሰጠው አገልግሎት የተዘጋጀ በስደት ሳለ ነበር፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ በስደቱ ጊዜ በብዙ አምላካዊ መገለጦችና ራዕዮች ተጎብኝቶ ነበር፡፡ ቅዱስ ዳዊትም በተሳደደ ጊዜ ‹‹ጎሥዐ ልብየ ቃለ ሰናየ ልቤ መልካም ቃልን አወጣ፡፡››የሚለውን መዝሙር፤ እንዲሁም ‹‹እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል፤ ዝምም አይልም›› የሚለውን ጻፈ፡፡ (መዝ 44፥1፣39፥3) ታላቁ ነቢይ ኤልያስም ወደ ቀርሜሎስ ተራራ በሸሸ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር አመልክቶ በአንድ ጊዜ ከአራት መቶ በላይ የበአል ነቢያትን አጠፋ፤ ወደ ንጉሡ በኃይል ይወስዱት ዘንድ ሁለት የሃምሳ አለቃ ጦር በየተራ በተላከበት ጊዜም ‹‹እሳት ከሰማይ ትውረድ›› በማለት ተናገረ፣ ገሰጻቸውም፡፡ (2ኛ ነገ 1፥10) ቅዱስ ጳውሎስም እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ የተወሰደውና ‹‹ሰው ሊናገራቸው የማይገቡ የማይናገሩ ቃላትን›› ወደ ሰማበት ወደ ገነት የገባው በዚህ ጊዜ ነው፡፡
; ለህዝቡ ያዘጋጀው የመግቦት መንገድ ነው
ምንም እንኳ አሳዳጆች ቅዱሳን የእግዚአብሔርን አገልግሎት እንዳይ ፈጽሙ በሄዱበት ቦታ እየተከታተሉ ቢያሳድዷቸውም እግዚአብሔር ግን ስደታቸውን ለበጎ አደረገ፡፡ አይሁድ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገድለው፣ በኢየሩሳሌም ወንጌል እንዳይሰበክ ክርስቲያኖችን ቢያሳድዱም ይህ ራሱ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም ውጪ ላሉ ሕዝቦች ያዘጋጀው የመግቦት መንገድ ሆነ፡፡ ‹‹የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ፡፡›› እንዲል፡፡ (ሐዋ 8፥4) የያዕቆብ ልጆች ወንድማቸው ዮሴፍን ለስደት በዳረጉት ጊዜ እግዚአብሔር የዮሴፍን ስደት የዓለምን ሕዝብ ከረሀብ ለማዳን ተጠቀመበት። ቅዱስ አትናቴዎስ አርዮሳውያንን ሸሽቶ ወደ ሮም በሄደበትና በዚያም በቆየበት ጊዜ የምዕራቡ ክፍል (ላቲን) በኦርቶዶክሳዊ እምነት እንዲጸናና እንዲጠነክር አደረገ፤ ምንኩስናና ገዳማዊ ሕይወትን አስተዋወቀ፡፡ ከእርሱ ጋር በግብጽ በረሃ ይኖሩ የነበሩ ሁለት መነኮሳት ነበሩና ።የእነርሱን አለባበስና አኗኗር ራሱ የቅዱስ እንጦንዮስ ደቀ መዛሙር እስኪባል ድረስ ገዳማዊ ከነበረው ከእርሱ ጋር ተደምሮ ምዕራባውያን ገዳማዊ ሕይወትን እንዲማሩ ዕድል ሰጣቸው፤ ይህም የእግዚአብሔር መግቦት ነው፡፡
; መንግሥተ ሰማያትን መውረስ (የመንግሥተ ሰማያት ተስፋ)
ጌታችን ‹‹ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና፡፡ ሲነቅፋአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ፡፡ ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ ሐሴትንም አድርጉ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና፡፡›› የሚል ተስፋን ሰጥቶናል፡፡ (ማቴ 5፥10-12) ይህን ተስፋ ማግኘት የሚችሉበት ግን መከራውን የሚታገሱት ናቸው፡፡ ‹‹መከራ ትዕግሥትን ያመጣል፣ ትዕግሥትም ፈተናን መላመድንና መቻልን፣ መላመድም ተስፋን ያደርጋል፣ ተስፋም አያሳፍርም፡፡›› እንዲል (ሮሜ 5፥4) መከራን መታገስ ብቻ ግን ይህን ተስፋ አያስገኝም፡፡ ጌታችን ‹‹የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው›› አላለም፤ ‹‹ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ›› አለ እንጂ፡፡ ‹‹ክፉውን ሁሉ ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ፡፡›› ብቻ አላለም ‹‹በእኔም ምክንያት››፣ ‹‹በውሸት›› የሚሉትን ጨመረ እንጂ፡፡ ስለዚህ ስለ እውነት ብለው የሚሰደዱ እውነተኞች፣ ስለ ክርስቶስ ብለው የሚነቀፉ፣ የሚሰደዱ ክርስቲያኖች ብፁዓን የተመሰገኑና የተባረኩ ናቸው፤ ዋጋቸውም በሰማያት ታላቅ ነው፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይወርሳሉና፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Comments
Post a Comment