የጥምቀት አስፈላጊነት
በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከኒቂያ ጉባኤ በኋላ ከተነሱት አባቶች አንዱ “በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም” ራእይ ፳፥፮ የሚለውን የወንጌላዊው ዮሐንስን አባባል በተረጎመበት የእግዚአብሔር ከተማ በሚለው መጽሐፉ ላይ ፊተኛው ትንሣኤ የተባለው ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና የምናገኝበት ጥምቀት እንደሆነ ገልጿል (De Civitate Dei,xx,6)፡፡
ክርስቶስን መሠረት ያደረገ እምነት ሁሉ “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ዮሐ. ፫፥፫ የሚለው የጌታ ትምህርት መመሪያው ሊሆን ግድ ነው፡፡ ጌታ እንዳስተማረውም ያለጥምቀት ድኅነት የለም፡፡
ጥምቀት በሚታየው አገልግሎት በውኃ ውስጥ ገብቶ መነከር፣ መዘፈቅ፣ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት ማለት ሲሆን በሚታየው አገልግሎት የሚገኘው የማይታይ ጸጋ ግን ብዙ ነው፡፡ የሚከተሉት በጥምቀት የሚገኙ የማይታዩ ጸጋዎች ናቸው፡-
ድኅነት
“ያመነ የተጠመቀ ይድናል” ማር. ፲፮፥፲፮፡፡ የድኅነት ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽ እንደተናገረው ዘላለማዊ ድኅነትን ለማግኘት የሚሻ ሁሉ ወልድ ዋሕድ በምትለው ሃይማኖት አምኖ መጠመቅ ግድ ይለዋል፡፡ ከጌታ ከቃሉ የተማረ ቅዱስ ጴጥሮስ የመምህሩን ትምህርት መሠረት አድርጎ “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፤ የእግዚአብሔር ትዕግስት በኖኅ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም፡፡ ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም” ብሏል፡፡ ፩ኛ ጴጥ. ፫፥፳-፳፩፡፡ ኖኅና ቤተሰቡ የዳኑበት ውኃ ምሳልነቱ የጥምቀት መሆኑን ገሌጾ አሁንም በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ያመኑ ሁሉ በጥምቀት ድኅነትን እንደሚያገኙ በግልጽ ቃል ተናግሯል፡፡
መዳን ስንል የእግዚአብሄርን መንግሥት ወርሶ የዘላለም ሕይወት ባለቤት መሆን ማለት ነው፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ አይሁድ ለነበረው ለኒቆዲሞስ ዘርግቶለት በነበረው የለሊት የትምህርት መርሐ ግብር ትምህርቱን በተመስጦ ኅሊና በሰቂለ ልቡና ይከታተል ለነበረው ለኒቆዱሞስ የድኅነት በሩ ጥምቀት እንደሆነ ገልጾለታል “እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሊገባ ይችልም” ዮሐ. ፫፥፭፡፡
ዳግም ልደት
ዳግም ልደት ያስባለው ከሥጋ ልደት የተለየ በመሆኑ ነው፡፡ በአዳምና በሔዋን ስህተት ምክንያት አጥተነው የነበረውን የልጅነት ጸጋ የምናስመልሰው በውኃ በምናደርገው ጥምቀት ነው፡፡ ዳግም ከሥላሴ የምንወለደው በውኃ በምናደርገው ጥምቀት ነው ጌታችን “እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም” ዮሐ. ፫፥፭ በማለት ለኒቆዱሞስ መናገሩን ልብ ይሏል፡፡ ጌታችን እንደተናገረው ጥምቀት የልጅነትን ጸጋ የምናገኝበት ምሥጢር ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ
ጴጥሮስ ጥምቀት ዳግም ከእግዚአብሄር የምንወለድበት ታላቅ ምሥጢር መሆኑን እንዲህ ሲል አስተምሯል “ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፉ ዘር አይደለም” ፩ኛ ጴጥ. ፩፥፳፫፡፡ ይህ ጥምቀት የዘላለም ሕይወት እንደሚያሰጥ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ደግሞ “ነፍሴም ስለ እርሱ በሕይወት ትኖራለች” አለ፡፡ መዝ. ፳፩፥፳፱"፡፡ አቡቀለምሲስ ዮሐንስም “እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ” ብሏል ዮሐ ፩፥፲፫፡፡
ጌታችን በግልጽ ቃል እንደተናገረው የልጅነት ጸጋ የሚገኘው በውኃ ውስጥ ብቅ ጥልቅ በማድረግ በሚፈጸመው ገቢር እንጂ አንዳንዶች ከልቦናቸው አንቅተው እንደሚናገሩት ቃለ ወንጌልን በመስማት ብቻ የሚገኝ አይደለም፡፡
ሥርየተ ኃጢአት
“ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት” የቁስጥንጥንያ አንቀጸ ሃይማኖት፡፡ በ381 ዓ.ም. በቁስጥንጥንያ በመቅዶንዮስ ክህደት ምክንያት ከመላው ዓለም የተሰባሰቡት 150 ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መቅዶንዮስን ካወገዙ በኋላ ባወጡት አንቀጸ ሃይማኖት ላይ ካሰፈሩት አንቀጽ አንዱ በጥምቀት ሥርየተ ኃጢአት እንደሚገኝ ነው፡፡ እነዚህ አባቶች በቅዱስ መጽሐፍ የሰፈረውን በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች አማካይነት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሾልኮ የገባን የስህተት ትምህርት ለማጥራት፣ እምነትን ለማጽናትና ምእመናንን ከውዥንብር ለመታደግ አንቀጸ ሃይማኖትን ወስነዋል፡፡
የአበው ውሳኔ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ መሆኑን ከሚከተሉት ማስረጃዎች እምንገነዘበው እውነታ ነው፡-
በድንቅ አጠራሩ ለአገልግሎት የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስ ከኃጢአቱ ይነጻ ዘንድ“አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ”መባሉን አስተውሉ፡፡ የሐዋ. ሥራ ፳፪፥፲፮፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሣ ተሰብስበው ለነበሩት አይሁድና ወደ ይሁዲ እምነት ለገቡት በትምህርቱ ልቡናቸው በተነካ ጊዜ “ምን እናድርግ?” ብለው ሲጠይቁት የመለሰላቸው “ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁ ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ” የሚውለን ነበር፡፡ የሐዋ. ሥራ ፪፥፴፯-፴፰፡፡ ይህ ታዲያ ከሌላ በረት ለመጡ በጎች እንጂ በበረቱ ተወልደው በበረቱ ላደጉት በጎች አይደለም፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ ማለቱ የእርሱን የባሕርይ አምላክነት ለመግለጽ እና ዓለም እንዲቀበለው ለማስተማር እንጂ ጥምቀት መፈጸም የሚገባው በሥላሴ ስም መሆኑን ጌታችን ራሱ አስተምሯል፡፡ ማቴ ፳፰፥፲፱፡፡
ክርስቶስን በሞቱ የምንመስልበትና በትንሣኤው የምንተባበርበት
“ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛ በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” ሮሜ. ፮፥፫-፬፡፡
ማጥመቅ በፈሳሽ ውኃ ነው፤ጥልቅ ውኃ በማይገኝበት ጊዜ ግን ውኃ በሞላበት ገንዳ ይፈጸማል ይህም ካልሆነ ውኃ ቀድቶ የተጠማቂውን መላ አካል ውኃው እንዲያገኘው በማድረግ በእጅ እየታፈኑ ያጠምቁታል፡፡
በጥምቀት ጊዜ የተጠማቂው አካል በውኃ እንዲጠልቅ መደረጉ “ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን” ሮሜ. ፮፥፬ የሚለውን በገቢር ለመግለጽ ነው፡፡ እንዲሁም ተጠማቂው ከውኃ ውስጥ ብቅ ማለቱ “በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ሥራ በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሳችሁ” ቆላ. ፪፥፲፪ ያለውን እንዲሁ በድርጊት ለማሳየት ነው፡፡
አጥማቂው ካህን “አጠምቀከ በስመ አብ አጠምቀከ በስመ ወልድ አጠምቀከ በስመ መንፈስ ቅዱስ” እያለ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እያደረገ ድርጊቱን ሦስት ጊዜ መፈጸሙ በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት አምኖ መጠመቁን ለማጠየቅ ሲሆን እንዲሁም የጌታን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በመቃብር አድሮ መነሳቱንና ተጠማቂዎችም ኋላ በትንሣኤ ዘጉባኤ ንቃ መዋቲ የሚለው አዋጅ ሦስት ጊዜ በሚታወጅበት ጊዜ በቀዋሚ አካል በምትናገር አንደበት ከራስ ጠጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው ከቁጥር ሳይጎድሉ ከሰውነታቸው ሳይከፈሉ ወንድ በአቅመ አዳም ሴት በአቅመ ሔዋን መነሳታቸውን ለማዘከር ነው፡፡
ስለዚህ “ከክርሰቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን” ሮሜ. ፮፥፰ በሚለው የሐዋርያው ቃለ ትምህርት መሠረት ጥምቀት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሞቱ የምንመስልበት በትንሣኤውም የምንተባበርበት ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡
የክርስቶስ አካል መሆናችን የሚረጋገጥበት
በዘመነ ብሉይ የአብርሃም ወገኖች የአብርሃም ልጆች መሆናቸው ይረጋገጥ የነበረው በግዝረት ነበር፡፡ግዝረት በኦሪቱ የእግዚአብሔር ሕዝብ መለያ ነበር፡፡ ያልተገረዘ ሁለ ከሕዝቡ ተለይቶ እንዲጠፋ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ነበር፡፡ ዘፍ. ፲፯፥፲፬፡፡
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በአምሳልነት ሲፈጸም የኖረው ግዝረት በዘመነ ሐዲስ በጥምቀት መተካቱን አበክሮ ያስገነዝባል “በክርስቶስ ገዛሪነት የኃጢአትን ሕዋስ ሰንኮፍ ቆርጦ በመጣሉ ሰው ሰራሽ ያይደለ ግዝረትን የተገዘራችሁበት፤በጥምቀት ከእሱ ጋር ተቀበራችሁ ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትም በሃይማኖት ከእሱ ጋር ለመኖር በእስዋ ተነሣችሁ” ቆላ. ፪፥፲፩-፲፪፡፡
ግዝረት ለሕዝበ እግዚአብሔር የአብርሃም የቃል ኪዲን ተሳታፊዎች የመሆናቸው መለያ ምልክት እንደነበር ሁሉ ጥምቀት ደግሞ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ የጸጋው ግምጃ ቤት ከሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው ጸጋ ተሳታፊ ያደርጋቸዋል፡፡
በጥምቀት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ እንሆናለን “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና” ገላ. ፫፥፳፯ በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው በጥምቀት ከእግዚአብሔር ጋር አንድ እንሆናለን፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ያደሰውን አዲሱን ሰውነት የምንለብሰውና የክርስቶስ ተከታዮች የምንሆነው በጥምቀት ነው፡፡ ግዝረት አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ ሁሉ ጥምቀትም አንዲት ናት፤ አትከለስም፣ አትደገምም፡፡ ኤፌ. ፬፥፭፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፡-
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅደሳን
የአሜሪካ ማዕከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል
፳፻፫ ዓ.ም.
Comments
Post a Comment