ምንኩስና ክፍል ፪

ለመሆኑ የመነኮሳቱ አመጋገብ እንዴት ነው?
      መነኮሳቱ የሚመገቡት፦ ቋርፍ ወይም ስራስር ተቆፍሮ የሚገኝ ንፍሮ፣ዳቤ ወይም መኮሬታ፣ ቅጠላ ቅጠል፣ ቆሎ የመሳሰሉትን እንደ ገዳሙ  ስርዓት መሰረት በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ዘጠኝ ወይም ሶስት ሰዓት ላይ ብቻ ይመገባሉ።
አለባበስ፦መነኮሳት በምድር መላእክት በሰማይ ሰዎች ናቸው ስለዚህ በዚህ  አስተሳሰብ ከዓለማዊያን እንደተለዩ ሁሉ በአለባበስም  እንዲሁ ይለያሉ ።
አለባበሳቸው መነኮሳት ቢጫ ወይም ወይባ መልክ ያለው፣ ጥቁርና የማር መልክ ያለው ምክንያቱም ከዓለም የተለዩ፣ ዓለምን ንቀውና ንፅህናቸውን ጠብቀው መኖርን  ስለመረጡ በሥጋ ደክመው በመንፈስ የበረቱ ማለት ሲሆን በዓለማውያን ዘንድ የተናቀ የተጠላ መልበሰን መረጡ የሚሉ አሉ።
        ከ644 ዓ/ም በፊት በግብፅ ውስጥ  ጥቂት አረማዊያን ቢኖሩም የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች በብዛት እንደነበሩ ታውቀዋል። እስላሞቹ የክርስትና እምነትህን ክደህ የእስልምና እምነት ያዝ እያሉ በሰይፍና በግርፋት እያስገደዷቸው እንዲሁም ንዋያተ ቅድሳቶቻቸውን እያቃጠሉ አብያተ ክርስትያኖቻቸውን እያፈረሱ  መስጊድ ይሰሩባቸው ስለነበር በዚህ ችግር ምክንያት ክርስትያኖች ምንም ጥቂት ቢሆኑም ከእስላሞቹ ጋር ጦርነት ገጠሙ በእግዚአብሔር ኃይልም ብዙውን ጠላት ቢጠርጉትም አረቦች እየተባበሩባቸው ተሸነፉ። ከዚም በኋላ እስላሞቹ በክርስትያኖች ላይ አሰቃቂ ደንብ አወጡ ።ከደንቦቹ አንዱ ክርስትያኖቹ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የማር መልክ  ያለው ልብስ እንዲለብሱ ነበር። በአሁኑም ጊዜ መነኮሳቱ ያንን የመከራ ዘመን ለማስታወስ የማር መልክ ያለውን ልብስ ይለብሳሉ።
የመነኮሳተ መመሪያ የገዳሙ ስርዓት፦
          የምንኩስና ህይወት በትሩፋት የበለፀገ ቢሆንም የሁሉም መነሻ የሚሆን መመሪያዎች አሉት። 
ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ፦  
1-ንጽሕና ቅድስና
2-መታዘዝ
3-ለግል የሆነ ሀብት አለማስቀመጥ
4-ጾም ስግደት ጸሎት ናቸው
        በመጨረሻም መነኮሳቱ ደረጃ በደረጃ ከሕገ ሥጋ ወደ ሕገ ነፍስ፣  ከወጣኒነት ወደ ማዕከላዊነት፣ ከማዕከላዊነት ወደ ፍጹምነት ማለት ወደ ዐሥሩ መዓርጋት ይደርሳሉ። ዐሥሩ መዓርጋትም እነዚህ ናቸው።
-ጽማዌ፡- መላእክት ሲወጡ ሲወርዱ ማየት፣ነገር ግን የሚወጡበትንና የሚወርዱበትን አለማወቅ ነው።
-ልባዌ መላእክት፦ የሚወጡበትንና የሚወርዱበትን ማወቅ ነው።
-ጣዕመ ዝማሬ፦ ከዚህ መዓርግ ሲደርሱ ውዳሴ ከንቱ ይቃወማቸዋል።
-አንብዐ ንስሓ፡- እንደሰን ውኃ እንባቸው ሳያቋርጥ መፍሰስ ነው።
-ኩነኔ፡- ሥጋን ለነፍስ ማስገዛት ነው።
-ዑቃቤ፡- በዚያው ጸንቶ መኖር ነው።
-ንጻሬ፡- ካሉበት ሁኖ መላእክትን በየከተማቸው ማየት።
-ሑሰት፡- እንደ እግረ ፀሐይ ከሁሉ መድለስ ነው።
-ተሰጥሞ፡- በባሕረ ብርሃን መዋኘት ነው።
-ፍቅረ ደቂቀ እጓለ እመሕያው፡- አማኒ መናፍቅ፣ ኃጥእ ጻድቅ፣ ባዕድ ዘመድ፣ ሳይሉ ሁሉን አንድ አድርጎ አስተካክሎ መውደድ                    ነው።
   ውድ አንባቢያን እኛም ሁላችን አባቶቻችን አስከ ዛሬው ትውልድ ድረስ ጠብቀው ያቆዩልንን የአነዚህ መነኮሳት ፀሎት አኛንም ሀገራችንን ኢትዮጵያን ይጠብቅ ዘንድ ለገዳሞቻችን ትኩረት ልናደርግና ልንደግፋቸው ይገባል።    
ምንጭ፦ የኢ/ኦ/ቤ/ክ ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻
ወስብሐት ለእግዚአብሄር

Comments

Post a Comment

Popular posts from this blog

ቅዱስ ያሬድ ማነው? ከዳንኤል ክብረት

መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ፬ የሐዲስ ኪዳን መግቢያ

መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ፪