መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ፩
መጽሐፍ ቅዱስ ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ቅዱስ ማጽሐፍ ማለት ነው፡፡ በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህን በተመለተ ‹‹ ቅዱሳን መጻሕፍት ›› የሚል ንባብ ይገኛል፡፡ ሁለቱን እንደሚከተለው እናያለን፡፡ 1. ‹‹ ….በነቢያቱ እና በቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ለሰጠው ወንጌል ለእግዚአብሔር ተለየ፡፡ ›› /ሮሜ 1.2/ 2. ‹‹ …. ከህፃንነትህ ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል ›› /2ጢሞ 3፡15/ ከስያሜው እንደምንረዳው መጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ነው፡፡ ቅዱስ የተባለበት ምክንያትም፡- 1. ቅዱስ ማለት የተለየ፣ ክቡር ማለት ሲሆን ከርኩሳንና ከተናቁ መጻሕፍት የተለየ ስለሆነ 2. ከቅዱስ እግዚአብሔር የተገኘ ቃልን የያዘ መጽሐፍ ስለሆነና ቃሉን የሚጠብቁትን ምዕመናንን የሚቀድስ ስለሆነ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ይህም ማለት ለሰው ዘር ሁሉ እውነተኛ የእግዚአብሔርን የማዳን መልዕክት የያዘ መጽሐፍ ነው ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃልም፡- 1. ዘለዓለማዊ ነው፡፡ /ኢሳ 40፡8፡፡ ማቴ 24፡35/ 2. የመንፈስ ሠይፍ ነው /ኤፌ 6፡17/ 3. የሚሠራ ሕያው ነው /ዕብ 4፡12/ 4. የሰው ልጆች ዳግመኛ የሚወለዱበት ከማይጠፋ ዘር ነው፡...