መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ፩


መጽሐፍ ቅዱስ ምንድን ነው?



  መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ቅዱስ ማጽሐፍ ማለት ነው፡፡ በራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህን በተመለተ ‹‹ቅዱሳን መጻሕፍት›› የሚል ንባብ ይገኛል፡፡ ሁለቱን እንደሚከተለው እናያለን፡፡

1.      ‹‹….በነቢያቱ እና በቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ለሰጠው ወንጌል ለእግዚአብሔር ተለየ፡፡›› /ሮሜ 1.2/

2.     ‹‹…. ከህፃንነትህ ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል›› /2ጢሞ 3፡15/

ከስያሜው እንደምንረዳው መጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ነው፡፡ ቅዱስ የተባለበት   ምክንያትም፡-
1.      ቅዱስ ማለት የተለየ፣ ክቡር ማለት ሲሆን ከርኩሳንና ከተናቁ መጻሕፍት የተለየ ስለሆነ
2.     ከቅዱስ እግዚአብሔር የተገኘ ቃልን የያዘ መጽሐፍ ስለሆነና ቃሉን የሚጠብቁትን ምዕመናንን የሚቀድስ ስለሆነ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ይህም ማለት ለሰው ዘር ሁሉ እውነተኛ የእግዚአብሔርን የማዳን መልዕክት የያዘ መጽሐፍ ነው ማለት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቃልም፡-
1.      ዘለዓለማዊ ነው፡፡  /ኢሳ 40፡8፡፡ ማቴ 24፡35/
2.     የመንፈስ ሠይፍ ነው /ኤፌ 6፡17/
3.     የሚሠራ ሕያው ነው /ዕብ 4፡12/
4.    የሰው ልጆች ዳግመኛ የሚወለዱበት ከማይጠፋ ዘር ነው፡፡ /1ጴጥ1፡23/
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎቹ ቃል ሳይሆን የአምላካችን የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ኅሊናችንን በማስገዛት ከልብ ልንታዘዝለት ይገባናል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ቅዱሳት መጻሕፍትን የያዘ የእግዚአብሔር የቃሉ መዝገብ ነው፡፡ በተለያዩ ሰዎች፣ በተለያዩ ቦታዎች፣ በተለያዩ ዘመናት፣ የተጻፉ ቅዱሳት መጻሕፍት በኋላ ዘመን በአንድነት ተሰብስበው የሚገኙበት መጽሐፍ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁሌም እርስ በእርሳቸው ሳይፋለሱ የሚናገሩት ለሰው ልጆች የተላለፈውን የእግዚአብሔርን መልዕክት ነው፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማ

መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለሰዎች የሰጠው የፍቅር መልእክት እንደ መሆኑ መጠን ዓላማው ሰዎችን የሚጠቅምና ሕይወትን የሚሰጥ የፍቅር ዓላማ ነው፡፡ የሚታየውንና የማይታየውን ድርጊት፣ በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር የሚሠራውን ሥራ ያስረዳል፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተሉትን ነገሮች ይዟል፡፡
1.      የእግዚአብሔር ሐሳብ
2.     የሰዎችን ሁኔታ
3.     የመዳንን መንገድ
4.    የኃጢአተኞችን ፍርድ
5.     የምዕመናንን ደስታ ይዟል፡፡
ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ ዓላማ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መግለጥ ነው፡፡ የእግዚአብሔርም ፈቃድ ሰዎች ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው  የዘለአለም ሕይወትን እንዲያገኙ /እንዲድኑ/ ነው፡፡
ይህንንም በሚከተሉት ጥቅሶች እንረዳለን፡፡

1.      ‹‹ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው /ዮሐ 6፡4ዐ/
2.     ‹‹….በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኗአል…›› /1 ቆሮ 1፡21/  
3.     ‹‹ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ አምናችሁም በስሙ የዘለዓለም ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ተጽፏል፡፡›› /ዮሐ 2ዐ፡31/

በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች እግዚአብሔርን በማፍቀር ለቃሌም በመታዘዝ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን የክብር ትንሣኤንና ዘላለማዊ ሕይወትን በተስፋ እንዲጠብቁ ልኳል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ቅዱስ ያሬድ ማነው? ከዳንኤል ክብረት

መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ፬ የሐዲስ ኪዳን መግቢያ

መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ፪